Sunday, September 22, 2024
spot_img

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከሕወሓት ጋር እስካሁን ድርድር እንዳላካሄደ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ የካቲት 15፣ 2014 ― ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕወሃት ጋር እስካሁን ድርድር እንዳልተካሄደ የተናገሩት በዛሬው እለት በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ነው፡፡

ከሕወሓት ጋር እስካሁን የተደረገ ድርድር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ስለድርድር ብዙ ሲወራ እሰማለሁ ግን እስካሁን ድርድር አላደረግንም፤ አላደረግንም ማለት እስከነአካቴው ድርድር የሚባል ነገር አይኖርም ማለት አይደለም›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም ‹‹ውይይት ማለት ችግር ተወግዷል ማለት ሳይሆን ችግር ለማስወገድ አማራጭ መንገድ አለው ወይ ብሎ ማየት ነው›› ያሉ ሲሆን፣ በድርድርም ኢትዮጵያን ነው የምናፀናው፣ በንትርክም ኢትዮጵያን ነው የምናፀናው በውጊያም ዋጋ የምንከፍለው ኢትዮጵያን ለማፅናት ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

 

የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሕወሓት እና መንግሥት መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ከሦስት ሳምንት በፊት ለመገናኛ ብዙሃን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ዶ/ር ደብረጽዮን ከቢቢሲ ኒውስ አወር ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት ድርድሩ የሚደረገው በአፍሪካ ኅብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በኬንያ አማካኝነት ነው፡፡

ሆኖም በዛሬው የፓርላማ ውሎ ድረድር አልተካሄደም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ‹‹ኢትዮጵያን ለማፅናት ሕይወታችንን ገንዘባችንን የምንገብር ከሆነ ኢትዮጵያን ለማፅናት ስሜቶቻችን አምቀን መነጋገር የሚቻል ከሆነ በደስታ ማየት ጥሩ ነው›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከእስር የተለቀቁ የሕወሓት ሰዎችን ክስ በድጋሚ ስለመቀጠል እንዲያጤን ከምክር ቤቱ አባል አቶ ክርስትያን ታደለ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ‹‹እነዚህ ሰዎች በመፈታታቸው ኢትዮጵያ ተጠቅማለች፡፡ የሚጠቅም ነገር ሲኖር ፕራግማቲክ መሆን ጥሩ ነው›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

በርካታ ጉዳዮች በተነሱበት የምክር ቤት ውሎ እሑድ እለት ኃይል ማመንጨት የጀመረውን የሕዳሴ ግድብ በተመለከተም የአባይ ግድብ በሚገነባበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ ያለው የጸጥታ መጓደል፤ የግንባታውን ሂደት ተፈታትኖት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሁለት ሳምንታት እንኳን በአካባቢው ጸጥታ የሚያስከበሩ ከአምስት በላይ ወታደሮች መገደላቸውን ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።

የተፈጸሙ ጥቃቶችን በተመለከለተም ‹‹ፋብሪካ ላይ መጥተው ሰው ያፍናሉ፤ ሲሚንቶ ጭኖ የሚሄድ ሾፌር ይገድላሉ። ሲሚንቶ ጭኖ የሚሄድ ሹፌር በፓትሮል ስናጅብ ደግሞ ፈንጂ ይቀብራሉ›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ሲሚንቶ ለማድረስ እንኳን ‹‹ፈተና›› እንደነበር አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የምክር ቤት ቆይታቸው በሕገ ወጥ የነዳጅ ንግድ የተሰማሩ ተሽከርካሪዎች እንዲወረሱ አዘዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እርምጃው የሚወሰደው ህገ ወጥ የነዳጅ ንግድን ለመከላከል በሚል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ‹‹ላለፉት ጥቂት አመታት ነዳጅ ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ደጉሟል›› ያሉት ዐቢይ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ለአካባቢው አገራት ነዳጅ የምታቀርብ አገር ሆናለች›› ሲሉ ህገ ወጥ ንግድ ችግር መፍጠሩን አስረድተዋል። ለዚህም ነጋዴዎችን እና የነዳጅ ዘይት ማመላለሻ ተሽከርካሪ ባለቤቶችን ከሰዋል።

አያይዘውም ‹‹የሁሉም ክልል ሚሊሺያዎች፣ ልዩ ኃይሎች ፖሊሶች ነዳጅ ከኢትዮጵያ ጭኖ የሚወጣ ቦቴ ካገኛችሁ ነዳጁን ብቻ ሳይሆን ቦቴውን ጭምር በመውረስ እንድትተባበሩን›› የሚል ጥሪ አቅርበዋል።

 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img