Sunday, September 22, 2024
spot_img

የሕወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ከተሞች በንጹሐን ዜጎች ላይ ግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን መፈጸማቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ ይፋ አደረገ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ የካቲት 9 2014 ― የሕወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ከተሞች በንጹሐን ዜጎች ላይ ግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን መፈጸማቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዛሬው እለት ይፋ ባደረገው ዐዲስ ሪፖርቱ ገልጧል፡፡

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ታጣቂዎቹ የአማራ ክልል ከተሞች በሆኑት በጭና እና ቆቦ ከተሞች እንዲሁም በአካባቢው በሚገኙ ሥፍራዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል ያለው ከነሐሴ 2013 እስከ መስከረም 2014 የመጀመሪያ ቀናት ድረስ ነው፡፡

አምነስቲ በሪፖርቱ ታጣቂዎቹ በአካል ላይ ካደረሷቸው ጥቃቶች በተጨማሪ የግድያ ማስፈራሪያዎች፣ ብሔር ተኮር ስድቦች እና ማንቋሸሾችን ማድረሳቸውንም ጠቁሟል፡፡

የሰብአዊ መብት ቡድኑ ይፋ ላደረገው ሪፖርት 27 የዓይን ዕማኞችን እና ከጥቃት የተረፉ እንዲሁም የሟቾችን አስከሬኖች በመሰብሰብ የቀብር ሥነ ሥርዐት የፈጸሙ ሰዎችን ማናገሩን አምልክቷል፡፡

አምነስቲ የትግራይ ኃይሎች በሰሜን ምሥራቅ አማራ በምትገኘው ቆቦ ከተማ ያልታጠቁ ሲቪል ሰዎችን ሆነ ብለው የገደሉት በአማራ ሚሊሻ እና በታጣቂ ገበሬዎች የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመበቀል ነው ብሏል፡፡

በጥቃቱ ላይ የተናገሩ የዓይን እማኝ በአካባቢው ንጹሐን መረሸናቸውን አስታውሰው፣ ከትምህርት ቤት አቅራቢያ በርካታ አስከሬኖችን ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከነዚህ መካከል 20 አስክሬኖች በውስጥ ልብስ ብቻ ነበሩ ብለዋል፡፡ አክለውም አብዛኛዎቹ ጭንቅላታቸውን፣ ሌሎቹ ኋላ እንዲሁም ከጀርባቸው በጥይት የተመቱ ስለመሆናቸው አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ከሐምሌ 2013 ጀምሮ በጭና እና በዙሪያዋ እድሜያቸው 14 የሚሆኑ ሴት ታዳጊዎችን ጨምሮ የትግራይ ኃይሎች በርካታ ሴቶችን በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ መድፈራቸውን እና አስገድደው ምግብ እንዲያበስሉላቸው ማድረጋቸውን አምነስቲ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

አምነስቲ ያነጋገራቸው 14 የጾታዊ ጥቃት ሰለባዎች በቡድን፤ አንዳንዶቹ ልጆቻቸው ፊት መደፈራቸውን ተናግረዋል። ለዚህ ማሳያ አንዲት የ7ኛ ክፍል ተማሪ እና 14 ዓመት ታዳጊ ከእናቷ ጋር በመኖሪያቸው ድር ባሕር ላይ መደፈሯን ለአምነስቲ ተናግራለች።

የአምነስቲ የምሥራቅ አፍሪካ ምክትል አካባቢ ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን የሕወሓት ኃይሎች በስፋት የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን፣ ግድያዎችን እና ከሆስፒታል ሳይቀር ዝርፊያ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ዳይሬክተሯ የሕወሓት አመራሮች በዚህ ወንጀል ተሳታፊ ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ አባላቱን ከጦሩ እንዲያስወግዱም ጠይቀዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሕወሓት ታጣቂዎች የተፈጸሙ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፤ አልያም የተማረኩ እስረኞች፣ እጅ የሰጡ ወይም የቆሰሉ ወታደሮችን መግደል ከጦር ወንጀል ጋር እንደሚስተካከል ምናልባትም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሊሆን እንደሚችል በሪፖርት አመልክቷል።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን ሪፖርት በተመለከተ ይህ ዘገባ እስከተሰናዳበት ሰአት ድረስ ከሕወሓት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img