አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ የካቲት 1፣ 2014 ― በኢትዮጵያ 20 የሚጠጉ የታሸገ ውሃ አምራቾች ሥራ ለማቆማቸው ሰበብ የሆነው የጥሬ ዕቃ እጥረት እንዲሁም የዋጋ ንረት መሆኑ ነው የተነገረው።
የታሸገ ውሃ ንግድ እያሽቆለ መሆኑን የጠቆሙት የኢትዮጵያ የታሸገ ውሃ፣ ለስላሳ መጠጥ፣ የአትክልትና ፍራፍሬዎች ማቀነባበሪያ ኢንዲስትሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ መርዕድ፣ በጥሬ እቃ ላይ ባለው የዋጋ ንረት ሰበብ አምራቾች በገበያው ላይ ለመቆየት ትግል ውስጥ ናቸው እንዳሉት ካፒታል ጋዜጣ አስነብቧል።
ዋና አስኪያጁ ለፋብሪካዎቹ ሥራ ማቆም ሰበብ የሆነውን የጥሬ አቅርቦት በተመለከተ ዋጋው በእጥፍ መጨመሩን ገልጸው፣ አሁን በገበያው ላይ ካሉት 20 የታሸገ ውሃ አምራቾች 20 ገደማ ሥራቸውን ሲያቆሙ፣ በገበያው ላይ ያሉት ፋብሪካዎች ደግሞ ከአቅም በታች እያመረቱ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
አያይዘውም የጥሬ እጥረቱ በዚህ ከቀጠለ በመዲናዋ አዲስ አበባ ጭምር የታሸገ ውሃ አቅርቦት እጥረት ሊገጥም እንደሚችል ነው የገለጹት።
ጨምረውም የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ጥበቃ ባስቀመጠው ክልከላ ምክንያት የታሸገ ውሃ አምራቾቹ ዋጋ መጨመር እንደማይችሉ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የአዲስ አበባ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገበያው ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበናል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 106 የውሃ አምራች ፋብሪካዎች ይገኛሉ።