Sunday, September 22, 2024
spot_img

የሶማሌ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የተወሰኑ አባላት በፓርቲው ውስጥ ተንሰራፍቷል ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመታገል የእርምት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አስታወቁ

  • “ኃላፊነት ተሰጥቷቸው፣ በሥራ አፈጻጸም ድክመትና በሙስና የተባረሩ ናቸው” የሶማሌ ክልል የኮሚኒኬሽን ምክትል ኃላፊ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 30፣ 2014 ― የሶማሌ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የተወሰኑ አመራርና አባላት በክልሉ ገዢ ፓርቲ የሆነው ፓርቲያቸው ውስጥ ተንሰራፍቷል ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመታገል የእርምት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ባወጡት መግለጫ አስታወቁ

የክልሉን ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ፣ የቀድሞ የካቢኔ አባላት፣ ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የዞን እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ያካተተው የሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ ክንፍ፣ መግለጫውን ያወጣው ትላንት ጥር 29፣ 2014 ነው፡፡

ቡድኑ በመግለጫው በ2010 በኢትዮጵያ ለውጥ ቢመጣም፣ የክልሉ ሕዝብ ግን ለዚህ አለመታደሉን በመግለጽ፣ ምክንያት ናቸው ያላቸውን ዘርዝሯል፡፡

ራሱን የሶማሊ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የእርምት ክንፍ የሚል ስያሜ የሰጠው ቡድን፣ ለእንቅስቃሴው በምክንያትነት ካስቀመጣቸው መካከል ‹‹ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ጥቅሞችን ማስቀደም፣ በበሳል ፖለቲካ መመራት አለመቻል›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በፓርቲው ውስጥ የግለሰቦች ሹመት ‹‹የፓርቲውን ሕገ ደንብ እና መመሪያ ያልተከተለ ነው›› ያለው ቡድኑ፣ ‹‹በጥቅም፣ በጋብቻ እና በጓደኝነት›› ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑም ጠቁሟል፡፡

ቡድኑ አክሎም የፓርቲውን አላማ ከማስረዳት አኳያ ቋሚ የምክክር መድረክ እንደሌለ ያነሳ ሲሆን፣ እየተቋቋመ የሚገኘውን አገራዊ የምክክር ሂደት የእጩዎች መረጣን በተመለከተም ግልጽ አለመሆኑን ጠቅሷል፡፡

የሶማሌ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የእርምት ክንፍ በመግለጫው ማሳረጊያ በክልሉ ያለው ለውጥ መንገዱን መሳቱን በመግለጽ፣ ወቅታዊ እና ተገቢ እርምት ካልተወሰደ ክልሉ ከማይወጣው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አዘቅት ውስጥ ሊዘፈቅ እንደሚችል አሳስቧል፡፡

ነገር ግን የቡድኑን መግለጫ አስመልክቶ ለሸገር ራድዮ የተናገሩት የሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሐመዴ ሻሌ መግለጫውን በማህበራዊ ሚዲያ ማየታቸውን ገልጸው፣ ግለሰቦቹ ከዚህ ቀደም በለውጡ ሰሞን ኃላፊነት ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ የተባረሩ ናቸው ብለዋል። በመግለጫው ላይ ከተሳተፉት መካከል አንዳንዶቹ የታገዱ መሆናቸውን ያነሱት ኃላፊው፣ አንዳንዶቹ በምርጫ ወቅት የኢዜማ እጩ እንደነበሩም ነው ያመለከቱት።

የሶማሌ ክልል የኮሚኒኬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሮብሌ በበኩላቸው እንደ ብልጽግና ኃላፊው ሁሉ ግለሰቦቹ ከዚህ በፊት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንደነበር በማስታወስ፣ አብዛኞቹ በሥራ አፈጻጸም ድክመትና በሙስና የተባረሩ ናቸው ብለዋል። አያይዘውም ፓርቲው መካከል የተፈጠረ ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በጉዳዩ ላይ መረጃ ይዞ የወጣው አዲስ ስታንዳርድ ድረ ገጽ፣ የቀድሞ የሶማሌ ክልል ባለሥልጣናት የነበሩ በርካታ ግለሰቦች በሆቴል በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ሊሳተፉ ሲሉ በቁጥጥር ስር ውለው ከአንደኛው በስተቀር መለቀቃቸውን አመልክቷል። ስብሰባውን ለመዘገብ የተገኙ ሦስት ጋዜጠኞችም ከታሳሪዎቹ መካከል እንደነበሩ ዘገባው ያመለክታል።

የሶማሌ ክልል የብልጽግና ጽሕፈት ዛሬ በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንደሚሰጥም ተሰምቷል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img