- ያለቀረጥ የሚገባው ሞባይል ስልክ በዚሁ ከቀጠለና ቁጥጥር ካልተደረገበት ሁለቱ የሞባይል መገጣጠሚያ ኢንዱስትሪዎችም በቅርቡ ይዘጋሉ ተብሏል
አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 30፣ 2014 ― በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመጣ የኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት 37 የተለያዩ የሞባይል ስልኮችን ከሚገጣጥሙ ፋብሪካዎች ውስጥ 35ቱ ተዘግተው ከገበያ ውጭ መሆናቸውንና ሁለት ብቻ መቅረታቸውን ያስታወቀው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡
መገጣጠሚያ ፋብሪካዎቹ የተዘጉት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ በድንበር የሚገባ ሞባይል ቀፎ የአገር ውስጥ ገበያውን በመቆጣጠሩ እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም አሁንም ያለቀረጥ የሚገባው ሞባይል ስልክ በዚሁ ከቀጠለና ቁጥጥር ካልተደረገበት ሁለቱ የሞባይል መገጣጠሚያ ኢንዱስትሪዎችም በቅርቡ ይዘጋሉ ብለዋል።
አቶ መላኩ ይህን የተናገሩት፣ ጥር 27 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚኒስቴሩን የስድስት ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢንዱስትሪና ማዕድንናት ጉዳዮች ቋሚ ኮሜቴ ባቀረቡበት ወቅት ነበር።
የአምራች ኢንዱስትሪው የቁልቁለት ጉዞ እየተጓዘ እንደሆነ የገለጹት አቶ መላኩ፣ ከፍተኛ ከሆነው የኮንትሮባንድ ግብይት በተጨማሪ በአምራች ኢንዱስትሪ የሚጠየቁ የመሬት አቅርቦት አለመኖር የመሠረተ ልማት አለመስፋፋት፣ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ረዥም የሆነ የቢሮክራሲ ማነቆና የሚያበረታታ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
በርካታ ማነቆዎች ያለው አምራች ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች በአሁኑ ጊዜ የሚያመርቱት ከ46 በመቶ አቅማቸው እንደማይበልጥ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኩባንያዎች ፋብሪካ እንዲገነቡ ሲታሰብ በሚገባ ባልተቀናጀ አሠራር እየተሄደ መሆኑን በመግለጽ ለአብነትም የሚከፈቱ ፋብሪካዎች ከግንባታው ቀድሞ ሊታሰብባቸው የሚገቡ የመሠረተ ልማትና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ከግምት ውስጥ ሳይገባ ሰፊ የሕዝብ ቦታ ላይ በአገር ሀብት ሕንፃ ተገንብቶ ለበርካታ ዓመታት ያለአገልግሎት እየቆመ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህ በአገር ውስጥ ባለ የዘፈቀደ አሠራር የተነሳ በውጭ ያሉ ኩባንያዎች መምጣት አይደለም በሥራ ላይ ያሉት አምራች ኢንዱስትሪዎችም ሥራ ሊያቆሙ እንደሚችሉ አመላክተዋል።