አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 30፣ 2014 ― የትግራይ ክልል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ከእናት ቤተ ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሶ ተዋህዶ ተነጠሎ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክሕነት ለመመሥረት መወሰኑን የዘገበው ለሕወሓት ቅርበት ያለው ድምጺ ወያኔ ነው፡፡
የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የሃይማኖት አባቶች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክተው ምክክር ማካሄዳቸውን የጠቀሰው ድምጺ ወያኔ፣ ሁሉም የትግራይ ሀገረ ሰብከት ያሳተፈ ቋሚ ጽሕፈት ቤት ለመመሥረት እና የቤተ ክርስትያንን ሕግ የማይቃረን የመተዳደርያ ደንብ ፀድቆ በሁሉም የትግራይ ክልል ሀገረ ሰብከቶች ቀርቦ እንዲታይ እንዲሁም ቀጥሎ በሚካሄደው ጉባኤ እንዲቀርብ የሚሉ እና ሌሎች ውሳኔዎች አስተላልፈዋል ብሏል፡፡
ዘገባው አክሎም የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶች በተለይ ‹‹ይወክለናል ያልነው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የተደረገላቸውን ተደጋጋሚ ጥሪ ወደ ጎን በማለት የትግራይ ጀኖሳይድ ላይ ደጋፊዎች ሆነዋል›› በማለት የራሳቸውን የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ሕህነት ለመመስረት መወሰናቸውን አመልክቷል፡፡
በትግራይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና ምእመናን በትግራይ ክልል በኢፌዴሪ መከላከያ፣ በሻእቢያና በአማራ ክልል ኃይሎች ደረሰ ያሉትን የምእመናን በደልና የቤተ ክርስቲያናት መፍረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቸል ብላለች ከመንግሥትም ጋር ወግናለች ብለው ሲከሱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለመመሥረት የመወሰኑን ጉዳይ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ቤትክርስትያን ቤተ ክሕነት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰአት ድረስ የሰጠው ማብራሪያ የለም፡፡