Sunday, September 22, 2024
spot_img

የኬንያው ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ውጊያ የገጠሙ ወገኖች ግጭቱን እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረቡ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥር 26 2014 ― የየጎረቤት አገር ኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ውጊያ የገጠሙ ወገኖች ግጭቱን እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ለተፋላሚ ወገኖች ጥሪውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ግጭት አስመልክተው ትላንት ምሽት ባወጡት መግለጫቸው ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በማስመልክት ባወጡት መግለጫ፤ ኬንያ ተኩስ ማቆምን እና ለመደራደር መንገድን ማመቻችት በሚሉ ጉዳች ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ያቀረቡትን ጥሪ እንደምትጋራ አስታውቋል፡፡

ጉተሬዝ ቀድመው ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ወገኖች የኦሎምፒክ መንፈስን ታሳቢ በማድረግ ግጭት በፍጥነት እንዲያቆሙ ተማጽኗቸውን አቅርበው ነበር። ዋና ጸሐፊው የጠቀሱት ስፖርታዊ ውድድር ነገ ዐርብ በቻይና ቤይጂንግ የሚጀመረውን የክረምት ኦሎምፒክን ነው።

የኬንያው ፕሬዝዳንት በመግለጫቸው በተመሳሳይ ሁኔታ የኦሎምፒክን መንፈስ አንስተው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በኦሎምፒክ መንፈስ ሰላምን እንዲቀበል እና ለእውነተኛ እርቅ መንገድ እንዲጠርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

እንደ ኬንያ ፕሬዝዳንት እና እንደ ወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ወዳጅ ጥሪውን ማቅረባቸውን የጠቀሱት ኡሁሩ፣ ሀገራቸውን በምትጎራበተው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው ያሉት ግጭት፤ በታላቂቱ አገር ባህል እና ስልጣኔ አብሮ የተሸመነውን ክብር ከሀገሪቱ ህዝብ ላይ መንሳቱን ቀጥሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ፣ ጸጥታ እና መረጋጋት ሊረጋገጥ የሚችለው በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ኃይሎች ፈተናዎችን ዘላቂ እና በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ ሲወጡ ብቻ እንደሆነም ኡሁሩ ኬንያታ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም በማመቻመች እና ሀሳቦችን በማስተናገድ የሚካሄድ ሁሉን አካታች ብሔራዊ ውይይት በዚህ ረገድ መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመው፣ ብሔራዊ ውይይቱ በመላው ኢትዮጵያ ተጽዕኖ ለደረሰባቸው ሰዎች የግጭትን ጫና ሊያቃልል እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ከሚያደረጉ መሪዎች መካከል መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img