Friday, November 15, 2024
spot_img

የመንግሥት ተቋማት ለሕዝብ የሚያቀርቡት መረጃ ትክክለኛነት የሚረጋገጥበት አስገዳጅ ሥርዓት እንዲዘረጋ ተጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥር 25፣ 2014 ― በርካታ የመንግሥት ተቋማት ለፓርላማው የሚያቀርቡት የአፈጻጸም ሪፖርትም ሆነ በሌላ በኩል ለሕዝብ የሚያደርሱት መረጃ ከአዘገጃጀቱ እስከ አቀራረቡ ድረስ የተዓማኒነት ችግር ያለበት በመሆኑ፣ መረጃው ደረጃውን የጠበቀ መሆኑንና ትክክለኛነቱን አስገዳጅ ሥርዓት እንዲዘረጋ ተጠይቋል፡፡

አገራዊ የልማት ዕቅዶችን፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለማዘጋጀት፣ ለመከታተልና ለመገምገም የሚረዱ አስተማማኝና ደረጃቸውን የጠበቁ ወቅታዊ መረጃዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ መረጃ አመንጪ ከሆኑ ተቋማት በመሰብሰብ፣ መረጃዎችን፣ የማጥራት ሥራ ለብሔራዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ኃላፊነት ቢሰጠውም፣ አስገዳጅ የሆነ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ የተቋማትን መረጃ ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንዳልቻለ ተገልጿል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ በተቋማት የሚታየው አጠቃላይ የመረጃ አዘገጃጀትና ጥራት ችግር ያለበት ከመሆኑም በላይ፣ እነዚህ ተቋማት ወደ ኤጀንሲው የሚያመጡት መረጃ ጥራቱና ደረጃው ታይቶና ተገምግሞ በድጋሚ አስተካክለው እንዲመጡ ተነግሯቸው ከሄዱ በኋላ፣ ተመሳሳይ የሆነ ችግር ያለበት መረጃ ይዘው እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፣ ኤጀንሲው መረጃን የማጣራትና የማደራጀት ኃላፊነት ቢሰጠውም፣ ተቋማትን የሚያስገድድበት ሥርዓት ባለመኖሩ ‹‹ለሥራችን ትልቅ ችግር ፈጥሮብናል፣ በመሆኑም ቋሚ ከሚቴው ያግዘን፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የመንግሥት ተቋማት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባም ሆነ በቋሚ ኮሚቴ እንዲገመገም የሚያቀርቡት ሪፖርት ትክክለኛነት ሳይረጋገጥ አቅርበው ከመሄድ ውጪ፣ መረጃውን ከየት አመጣህ ብሎ የሚጠይቅ አካል አለመኖሩን አብራርተዋል፡፡

‹‹ሁሉም ተቋም አፈጻጸሜ ነው ብሎ አቅርቦ ይሄዳል፣ ነገር ግን የሚረጋገጥበት አሠራር የለም፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በመረጃ ሰጪውና ተቀባዩ መካከል ባለው ግንኙነት አንድ ተቋም የተሳሳተ መረጃ ሲያቀርብ፣ ወዲያውኑ ተጠያቂ የሚያደርግ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አክለው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ተቋማት ስለሚሠሩት ሥራ መረጃ ለመስጠት ፍላጎት ስለሌላቸው፣ ከደረጃ በታች የሆነ መረጃ የመላክ አባዜ የተጠናወታቸውን አካላት ከዘመኑ ጋር የሚሄድ መረጃ ለማግኘት የሚረዳ አሠራር እንዲዘረጉ ጠንካራ የሆነ ሕግና ሥርዓት እንዲዘጋጅ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ቢራቱ ይህን የተናገሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰኞ ጥር 23፣ 2014 የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የዘላቂ ልማት ግቦች መረጃዎችን ለማደራጀት ያደረገውን ዝግጅት አፈጻጸም ክዋኔ ኦዲት ላይ ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

በመረጃ አሰጣጥ በአገር ደረጃ እየታየ ያለው ችግር አስገዳጅ በሆነ ሕግ ካልታሰረ በስተቀር፣ ኤጀንሲው የትኛውንም ተቋም በአገራዊ ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ግምገማ ለማድረግ መረጃ ሲጠይቅ መረጃ አያገኝም፣ ወይም በሚፈለገው ደረጃና ጥራት እየቀረበለት እንዳልሆነ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል መባሉን የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img