አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥር 25፣ 2014 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት አርዳ ጅላ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሕይወትና የአካል ጉዳት ስለመድረሱ በደረሰው ጥቆማ መሰረት፣ ከታኅሣሥ 7 እስከ ታኅሣሥ 12፣ 2014 በቦታው በመገኘትና ተጎጂዎችን፣ የአይን እማኞችን፣ የሟች ቤተሰቦችንና የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት በማነጋገር ምርመራ ማካሄዱን ገልጧል፡፡
ኮሚሽኑ ምርመራውን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት በፀጥታ አባላት ቁጥጥር ስር የዋሉ የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16 ሰዎች ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው፣ 14ቱ ሰዎች በጥይት ተመተው መገደላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ኅዳር 21፣ 2014 ለስራ ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሄደው ከቀኑ 8 ሰዓት አከባቢ ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ የነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ በወረዳው ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኢፍቱ በተባለ ቦታ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የ11 ፖሊስ አባላት ሕይወት ማለፉና ቢያንስ 17 ሌሎች የፖሊስ አባላት መቁሳለቸው ጠቅሷል፡፡
ይህን ተከትሎ ኅዳር 22፣ 2014 በግምት ከቀኑ ሰዓት ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ በፈንታሌ ወረዳ ጡጢቲ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ዴዲቲ ካራ ከሚባል የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጅላ አባላት የመኖሪያ ሰፈር የደረሱ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የአይን እማኞች ጠቅሶ ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡
ኢሰመኮ ዛሬ ጥር 25፣ 2014 ይፋ ያደረገው ሪፖርት ከእነዚህ በፀጥታ አባላት ቁጥጥር ስር የዋሉ የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16 ሰዎች ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው፣ 14ቱ ሰዎች በጥይት ተመተው መገደላቸውን ነው የገለጸው፡፡
በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ መሬት ላይ እንዲተኙ ተደርገው በጥይት ተመተው መገደላቸውን የጠቀሰው የከረዩ አባገዳ ከዲር ሀዋስን ጨምሮ ኦዳ ጫርጨር፣ ቦሩ ፈንታሌ፣ ፈንታሌ ቦሩ፣ ቁምቢ ጉራቻ (ቃሉ ናቸው)፣ ቦሩ ፈንታሌ፣ ቡላ ፈንታሌ፣ ሮባ ሀዋስ፣ ቦሩ ጎዳና፣ ጂሎ ደዲኦ፣ ቡላ ፈንታሌ፣ ቡልጋ ቦረኡ፣ ጂሎ ዲዶ እና ቦሩ ጂሎ ናቸው፡፡ ከነዚህ ሰዎች ውጭ 2 ሰዎች ደግሞ ወደ ጫካ በመሮጥ ማምለጣቸውን ኮሚሽኑ ከምስክሮች ሰምቻለሁ ብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሟቾችን አስከሬን ለማንሳት ግድያው ወደ ተፈጸመበት ቦታ የሄዱ ሰዎች በቦታው በነበሩ ፖሊሶች እንዳያነሱ በመከልከላቸው፣ አስከሬኖቹ ለበርካታ ሰዓታት ሳይነሱ መቆየታቸውንና የፈነዱና በከፊል በዱር እንስሳ የተበሉ ጭምር እንደነበሩ አስከሬኖቹን ያነሱና የቀበሩ ሰዎች መግለጻቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ እንዲሁም አስከሬኖቹ ከጀርባ በኩል ወገባቸውና ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመተው መገደላቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች የነበሩባቸው መሆኑን እንደሚያስረዱ ተጠቅሷል፡፡
በእለቱ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ተይዘው ከተወሰዱት 39 የጅላ አባላት መካከል 23ቱ ወዴት እንደተወሰዱ ሳይታወቅ ቆይቶ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ጅሎ ቦረዩ የተባለ የጅላ አባል ሕይወቱ አልፎ አስክሬኑ በሞጆ ከተማ ከሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ለቤተሰብ መሰጠቱን ያመለከተው ኮሚሽኑ፣ በአስክሬኑ ጭንቅላት ላይ የመፈንከት፣ በተለያዩ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ ቁስል እና የድብደባ ምልክቶች ይታዩ እንደነበረ አስክሬኑን የተቀበሉ የቤተሰብ አባላት መግለጻቸውም ነው የተመላከተው፡፡ የተቀሩት በእሰር ላይ የነበሩ የጅላ አባላት ከሳምንታት በኋላ ከእስር ተለቀዋል ነው የተባለው።
ኢሰመኮ በምርመራው በሰበሰባቸውና ባገናዘባቸው ማስረጃዎች 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በኅዳር 22፣ 2014 በመንግስት የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በግዳጅ ወደ ጫካ ቦታ ተወስደውና የፀጥታና የአካባቢ አስተዳደር ሰዎች ባሉበት፣ ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት ተመተው የተገደሉ መሆኑንና ይህም ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ ስለመሆኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ሆኖ ማግኘቱን ገልጧል። በተጨማሪም፣ በግዳጅ ከተወሰዱት 23 የጅላ አባላት መካከል አንድ ሰው ሞጆ ከተማ በሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ በቁጥጥር ስር እያለ ሕይወቱ አልፎ ያለምንም ምርመራ አስክሬኑን ቤተሰቦቹ እንዲወስዱና እንዲቀበር መደረጉ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ተጨማሪ ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ መኖሩን በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ ሆኖ ማግኘቱን አክሏል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ይህን የግድያ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎችን እንዲሁም በፖሊስ አባላት ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች በሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ አስታውሰው፣ ‹‹ስለ ጠቅላላ የነገሩ ሁኔታ እውነቱን በመግለጽ፣ ፍትሕ በማረጋገጥና የተጎዱ ሰዎችን በመካስ ላይ የተመሰረተ አስፈላጊ ተግባራትን በማከናወን የማኅበረሰቡን ሰላም እና ደኅንነት እንዲመለስ ማድረግ ይጠበቃል›› ብለዋል።
በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ድብደባ እና ከሕግ ውጪ የሆነ ግድያ የፈጸሙና ያሰፈጸሙ የአስተዳደርና የፀጥታ አባላት ተገቢው የወንጀል ምርመራ ተደርጎባቸው በሕግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የጠየቀው ኢሰመኮ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለሟቾች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ለደረሰባቸው ጉዳት ተገቢ የሆነ ካሳ እንዲከፍል እና በስራ ላይ እያሉ የተገደሉና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው የፖሊስ አባላት ላይ የወንጀል ጥቃት የፈጸሙ ሰዎችን በሚመለከትም ተገቢውን የወንጀል ምርመራ በማድረግ በሕግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ብሏል፡፡
የከረዩ አባ ገዳ ከድር ሃዋስ ቦሩን ጨምሮ በበርካታ ግለሰቦች ላይ ለተፈጸው ግድያ ኅዳር 24፣ 2014 በመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች መግለጫ ያወጣው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ‹‹አሰቃቂ›› ያለውን ግድያ የፈጸመው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ‹ሸኔ› ነው ማለቱ ይታወሳል፡፡ ቢሮው በመግለጫው ቡድኑ በየቀኑ ንፁሃንን በአሰቃቂ ሁኔታ እየገደለ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያለውን ጭካኔ እያረጋገጠ ይገኛል ያለ ሲሆን፣ ጥቃቱን ካስተናገዱት መካከል ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ እና ሀደ ስንቄዎች እንደሚገኝበትም በመግለጫው አትቶ ነበር፡፡