Thursday, November 21, 2024
spot_img

መንግሥት ከሕወሓት ጋር አልተነጋገርኩም አለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥር 25 2014 የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕወሓት ጋር አለመነጋገሩን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሠ ቱሉ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ምላሽ የመጣው ባለፈው ቅዳሜ ከቢቢሲ ኒውስ አወር ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ከመንግሥት ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር መጀመራቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ዶ/ር ደብረጽዮን በቃለ ምልልሱ ላይ እንደተናገሩት ንግግሩ እየተካሄደ የሚገኘው በአፍሪካ ኅብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በኬንያ አማካኝነት ነው፡፡

ሆኖም መንግስት ‹‹ሰላምን ለሚያመጣ የትኛውም አማራጭ በሩን አይዘጋም›› ያሉት ዶክተር ለገሠ ቱሉ፣ ነገር ግን መንግስት ‹‹ከሕወሓት ጋር ቁጭ ብሎ አልተነጋገረም፤ በዚህ በኩል እንደ መንግስት የምናውቀው ነገር የለም›› ሲሉ ለዶይቸ ቬለ አስረድተዋል፡፡

የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን በበኩላቸው ጦርነቱን ለማስቆም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተደረገ ያለው ቀጥተኛ ያልሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት እያሳየ መሆኑንና የመሻሻል ምልክቶች እንዳሉ አመልክተው ነበር፡፡

የመንግስት እና ሕወሓትን ንግግር በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ለአምስት ሰዓታት የዘለቀ ውይይት አድርገዋል የተባሉት አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ መስፍን ተገኑ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን ነግረውኛል ማለታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ሆኖም ይህን መረጃ ተከትሎ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተመሳሳይ አስተባብለው ነበር፡፡

ባለፉት ሳምንታት ጋብ ብሎ የነበረውና 15 ወራት ያስቆጠረው በመንግስት እና በሕወሓት መካከል የሚካሄደው ጦርነት፣ ከሰሞኑ ዳግም በአፋር በኩል ማገርሸቱን የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ያገረሸውን ጥቃት በተመለከተ ከቀናት በፊት ሕወሓት ባሠራጨው መግለጫ፣ በአፋር ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አወል አርባ ልዩ ፖሊስና በኤርትራ መንግሥት ይደገፋል ባለው ‹‹የቀይ ባህር አፋር ኃይል›› ሲል በጠራው ኃይል ላይ ጥቃት መክፈቱን አሳውቋል፡፡

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሠ ቱሉ በበኩላቸው ሕወሓት የጠቀሰውን ክስ አጣጥለውታል፡፡ በሥፍራው በተለይ የኤርትራ ኃይል ለጥቃት አለመንቀሳቀሱን አመልክተዋል፡፡ በአፋር እና ትግራይ ድንበር በአባአላ እና በራህሌ መኖሩን የጠቆሙት ዶክተር ለገሠ፣ በሥፍራው ሕወሓት በከባድ መሳሪያ ጥቃት እንደሚሰነዝር በማንሳት፣ የተቆጣጠራው ወረዳ እንደሌለም ቢናገሩም፣ ሕወሓት በሥፍራው የተወሰኑ ወረዳዎችን ተቆጣጥሯል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img