Sunday, November 24, 2024
spot_img

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ዲና ሙፍቲ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ሊደራደር ነው መባሉን አስተባበሉ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥር 20 2014 ― የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ከሰሞኑ መንግሥት ከሕወሓት ጋር ሊደራደር ነው በሚል ስለተነገረው መረጃ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ረቡዕ ጥር 18፣ 2014 በኢትዮጵያ ጉዳይ ዘገባ ይዞ የወጣው አሶሽየትድ ፕረስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከሕወሓት ጋር ድርድር እንደሚያደርግ መናገራቸውን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

የዜና ወኪሉ ይህንኑ ለአምስት ሰዓታት የዘለቀ ውይይት አድርገናል ያሉት የአሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ መስፍን ተገኑ እንደነገሩት ነበር ያመለከተው፡፡

ነገር ግን በትላንትናው እለት መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ዲና፣ ጉዳዩ ምን ያህል እውነት ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹መንግሥት እስካሁን ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር እንደሚደራደር አላሳወቀም›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

መንግስት ህወሓትን አሁንም ቢሆን በሽብርተኝነት ነው የሚመለከተው ያሉት አምባሳደሩ፣ ድርድር ሊደረግ ነው የሚለው መረጃ ትክክል ያልሆነ እንዲሁም ከመንግስት በኩል የወጣ አለመሆኑንም ገልፀዋል።

በዘገባው አቶ መስፍን ተገኑን የጠቀሰው አሶሽየትድ ፕረስ በበኩሉ፣ በነበራቸው ቆይታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ድርድር እንደሚኖር ጠቁመው፣ ‹‹በርግጥ ይህ እንዲሆን ሌላኛው ወገንም ፍቃደኛ መሆን አለበት›› ስለማለታቸውም ተመላክቷል፡፡ አክለውም ‹‹የአገሪቱን ጥቅም የሚያስቀድም ምክንያታዊ ድርድር ይኖራል›› ብለዋል ነው ያለው፡፡

 

በመንግስት እና በሕወሓት መካከል የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት 15 ወራት አስቆጥሯል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img