Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአፋር ክልል ሕወሓት በኪልበቲ ረሱ ዞን በአብአላና በመጋሌ ወረዳዎች ጦርነት ከፍቶብኛል አለ

  • የሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በአብአላ ጥቃት የተቀሰቀሰው በአፋር ኃይሎች እና የኤርትራ ጦር ነው ሲሉ ከስሰዋል


አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥር 17 2014 የአፋር ክልላዊ መንግስት ሕወሓት በኪልበቲ ረሱ ዞን ውስጥ በሚገኙት በአብአላና በመጋሌ ወረዳዎች ጦርነት ከፍቶብኛል ሲል ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

የክልሉ መንግስት ሕወሓት ጦርነቱን የከፈተው ‹‹የደረሰበትን ከባድ ሽንፈት ለማካካስ›› መሆኑን የጠቀሰ ሲሆን፣ ለማሳያነት ትላንት ጥር 16፣ 2014 በኪልበቲ ረሱ ዞን በአብአላ፣ በመጋሌ እና በበራህሌ በኩል ‹‹በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት በመክፈት በርካታ ንፁሐንን›› ለጉዳት መዳረጉን ገልጧል፡፡

በመግለጫው የትግራይ ህዝብ ‹‹እብደት›› ሲል የገለጸውን የሕወሓትን ድርጊት ‹‹በቃህ ሊል ይገባል›› ያለው የአፋር ክልል፣ ‹‹ለጥቂት የቡድኑ አባላት ጥቅም ሲባል የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን መገበር›› እንደማይገባቸውም ነው ያሳሰበው፡፡

የአፋር ክልል ሕወሓት በአብአላና እና ሌሎች ወረዳዎች ጦርነት ከፍቶብኛል ማለቱን ተከትሎ የሕወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት ጌታቸው ረዳ ትላንት ጥር 16 በትዊተር ባሰፈሩት መልእክት፣ ጦርነቱን ቀድመው የከፈቱት የአፋር ኃይሎች ከኤርትራ ጦር ጋር ባንድነት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ሕወሓት በአብአላ በኩል ከፍቷል በተባለው ጥቃት ምክንያት ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይዘው ወደ መቀሌ እየተጓዙ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ወደ ኋላ መመለሳቸውን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሠላማዊት ካሣ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል፡፡ ይህ አካባቢ በዋናነት ወደ ትግራይ እርዳታ እንደሚተላለፍበት የገለጹት ወይዘሮ ሠላማዊት፣ ሕወሓት ግን ሆን ብሎ አካባቢውን አጥቅቷል ብለዋል፡፡

ከሚኒስትር ዲኤታዋ ቀደም ብሎ በትዊተር ገጻቸው ላይ የጻፉት የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከሰመራ ታጅበው ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ 27 መኪኖች ወደ ትግራይ ሊገቡ እንደነበር ገልጸው፣ ሆኖም የአፋር ክልል ጦርነት በመኖሩ መከልከሉ እንደ ማስተባበያ መቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ መንግስት ሳያውቀው ይፈጸማል የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለጹት ጌታቸው፣ ለሕዝባችን ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እንፈልጋለን፤ ለጥቃቅን ጀብዱዎች ፍላጎት የለንም ያሉ ሲሆን፣ አያይዘውም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ትኩረት አልሰጠንም ሲሉ ቅሬታ ሰንዝረዋል፡፡

ነገር ግን እንደ መንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዲኤታዋ ሁሉ የአፋር ክልል የአዳሮ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዐብዶ አሊ ሕወሓት አካባቢውን እንኳን እርዳታ፣ ተሸከርካሪ እግረኛ እንዳያልፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ጦርነቱንም የቀሰቀሰው ሕወሓት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጥቃቱ የደረሰውን በተመለተም ወይዘሮ ሠላማዊት ካሣ ወደ ሃምሳ ሺሕ የሚጠጉ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለአሜሪካ ድምጽ የተናገሩ ግለሰብ፣ ሕወሓት በአብአላ በስድስት ግንባር፣ በበርሃሌ ወረዳ አሰዳ የምትባል ግንባር እና በመጋሌ ሁለት ቦታ ጥቃት ከፍቷል ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ከባድ መሣሪያ እየተኮሱ መሆኑን በመጥቀስ፣ አብአላን ሙሉ በሙሉ እና በመጋሌ ሦስት ቀበሌዎች መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img