አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥር 12፣ 2014 ― በርዝማኔውና በኢትዮጵያ የሕንጻ ግንባታ ታሪክ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት መሆኑ የተነገረለት በዘመናዊ ጥበብ የታነፀው የንግድ ባንክ ሕንጻ ግንባታ በመጠናቀቁ በይፋ ሊመረቅ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው፣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምሥራቅ አፍሪካ ረዥሙ በመሆን የሚጠቀሰው የባንኩ ሕንጻ በይፋ የሚመረቀው ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው፡፡
ጥር 21፣ 2007 48 ፎቆች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲሱ ሕንጻ ግንባታ ሲጀመር ግንባታው 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንደሚጠናቀቅ ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ግን አጠቃላይ ወጪው ከሰባት እስከ ከስምንት ቢሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የሕንጻው ግንባታ ከተያዘለት ጊዜ በላይ መውሰዱ፣ የግንባታ ዕቃዎች መጨመር፣ የምንዛሪ ተመን ጭማሪና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች የግንባታውን ወጪ ከታሰበው በላይ እንዲሆን እንዳደረጉት ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዲዛይን ለውጥ ተደርጎ አዳዲስ ሥራዎች የታከሉ በመሆናቸው፣ መጀመርያ ከተያዘው ዋጋ በላይ ጭማሪ ማስከተሉ ተጠቁሟል፡፡
የሕንጻው ግንባታ ሲጀመር 46 ፎቆች ይኖሩታል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ግንባታው ከተጀመረ በኋላ ግን ሁለት ፎቆች ተጨምረዋል፡፡ እነዚህ ተጨማሪ ሁለት ፎቆች ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ጠይቀዋል ተብሏል፡፡ ከተጨማሪዎቹ ፎቆች 47ኛው ለሬስቶራንት አገልግሎት፣ 48ኛው ደግሞ አዲስ አበባን ከአራቱም አቅጣጫ ለማሳየት እንደገና ዲዛይን ተደርጎ ተገንብተዋል፡፡
በአገሪቱ የሕንፃ ግንባታ ታሪክ በዚህን ያህል ወጪ የወጣበት ሕንፃ እንደሌለ የታወቀ ሲሆን፣ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት የተገነባ እንደሆነ የሚጠቀሰው የአፍሪካ ኅብረት ሕንፃ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 48 ፎቆች ካሉት የዋናው ሕንፃው በተጨማሪ፣ ስድስትና ስምንት ፎቆች ያሏቸው ሁለት ተደራቢ ሕንፃዎችን ያካተተ ሲሆን፣ አንደኛው ተደራቢ ሕንፃ የስብሰባ አዳራሾችን የያዘ ነው፡፡ ሌላው ተደራቢ የሕንፃ ክፍል ደግሞ ለተለያዩ የንግድ ሥራዎች ማለትም ሬስቶራንቶችን፣ የንግድ ሱቆችንና ስድስት ያህል ሲኒማ ቤቶችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ዋናው ባለ48 ፎቅ ሕንፃ ከሦስተኛ እስከ 46ኛ ያለው ለባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ግልጋሎት የሚውል እንደሆነ፣ አንደኛውና ሁለተኛው የሕንፃው ፎቆች ደግሞ የባንኩን ታሪክ የሚያመላክቱ የማሳያ ሥፍራዎች እንደሚሆኑ፣ ከምድር በታች አራት ፎቆች ደግሞ ለ1 ሺሕ 500 መኪኖች ማቆሚያነት ያገለግላሉ ተብሏል፡፡
የንግድ ባንክን ሕንፃ ግንባታ ያከናወነው የቻይና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪነግ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ የማማከር አገልግሎቱን እየሰጠ የሚሰጠው ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡