አምባ ዲጂታል፣ ረዑዕ ጥር 11፣ 2014 ― በአማራ ክልል መቀመጫ ባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ቢሮ አጥር በጥምቀት በዐል ዋዜማ በታዳሚያን መፍረሱን የምክር ቤቱ ጸሐፊ ሐጅ ዑስማን ዑመር ገልፀዋል።
እንደ ጸሐፊው ከሆነ ከአጥሩ መፍረስ በተጨማሪ ከታዳሚያን የተለያዩ ክብረ ነክ ስድቦች መሰንዘሩን አሳውቀዋል።
ሐጅ ዑስማን በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ተከባብሮና ተቻችሎ በመኖር ብቻ ሀገር እንደሚገነባ ፅኑ እምነት ያላቸው የ[ክርስትና] እምነት ተከታዮች ድርጊቱን ሊያወግዙና አፀያፊ ባሉት በዚህ ተግባር የተሳተፉ አካሎችን “ወደ ህግ ማቅረብ” አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል እየተከበረው በሚገኘው የጥምቀት በአል ላይ የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው አካሎች በሙስሊሙና በኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታዮች በኩል ሆን ብለው በተመሳሳይ መልኩ ግጭት በመቀስቀስ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ ሀይሎች ስለሚኖሩ” ከምንጊዜውም በላይ የሁለቱም ሀይማኖት የአምልኮ ቦታዎች ጥብቅ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።
ዋና ጸሐፊው የሚመለከታቸው የክልልና የከተማው የፀጥታ መዋቅሮችም ከምንግዜውም በላይ ህገ መንግስታዊ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡና በባህርዳርም ሆነ በክልሉ በሚገኙ ከተሞችና ወረዳዎች አስፈላጊውን ጥበቃና ክትትል እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።