Friday, November 15, 2024
spot_img

የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለኤክስፖርት የሚቀርበው ቡና ከምርት ገበያ ውጭ ባለው ቀጥተኛ ሥርዐት እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥር 10፣ 2014 ― የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ለኤክስፖርት የሚቀርበውን ቡና ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ (ECX) ውጭ ባለው ቀጥተኛ የግብይት ሥርዐት ማለትም ከአቅራቢዎች ወይም ከገበሬዎች በቀጥታ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል፡፡

ካፒታል ጋዜጣ ይዞት በወጣው ዘገባ እንዳመለከተው፣ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ግብይቱ እንዲካሄድበት የወሰኑት ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሳይገባ ከገበሬው አልያም ከአቅራቢ ጋር የሚደረገው የቀጥታ ግብይት፣ ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን ከኤሌክትሮኒክ ግብይቱ ጎን ለጎን እንደ አማራጭ የጀመረው ነው፡፡

በጋዜጣው ዘገባ እንደተመላከተው፣ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ሰዎች ይኸው የቀጥታ ግብይት ኤክስፖርት የሚደረገውን ቡና መጠን እና ዋጋ ከመጨመሩ በላይ ገበሬውን ይበልጥ አትራፊ አድርጎታል ብለው ያምናሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አዱኛ ደበላም በተያዘው የበጀት ዓመት ባለፉት አምስት ወራት የተካሄደውን ግብይት በማንሳት ስኬታማ ለመሆኑ ሥርዐቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በከፍተኛ ደረጃ ያሉ ኃላፊዎች በክልሉ የሚመረተውን ቡና ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውጭ ግብይት እንዲደረግበት ተስማምተዋል ነው የተባለው፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ከሳምንታት በፊት አዳማ ላይ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቀን በተከበረበት ወቅት የተናገሩት የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ ዐብዲሳ፣ ለተሰብሳቢዎቹ ማኅበሮችን አቋቁሞ ገበሬዎችን እኩል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ቡናን በምሳሌነት በማንሳትም ባለፉት ሶስት ዓመታት ‹‹ኢሲኤክስ የሚባል ዘራፊ ድርጅት ላያችን ላይ አቋቁመው ሲዘርፉን ነው የነበሩት›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ርእሰ መስተዳደሩ አክለውም ‹‹ገበሬዎቻችን ሁለተኛ ለኢሲኤክስ እንዳትሸጡ›› ሲሉ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

ሆኖም አሁን የኦሮሚያ ክልል አካሄደዋለሁ የሚለው ሥርዐት ላይ አንዳንድ ለጉዳዩ ቅርብ በሆኑ ሰዎች ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ ይህ የቀጥታ ሥርዐት ግብይቱ በአንድ ማእከል መሆኑን በማስቀረት እንዲበተን ማድረጉን የሚጠቅሱት እነዚሁ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ሰዎች፣ ሥርዐቱ ለመንግስት ከግብር ሊያገኘው የሚገባውን የተወሰነ ገንዘብ እንዳያገኝ የሚያደርግ እንዲሁም በተመሳሳይ ዋጋ ላይ ችግር ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ከተመሠረተ አስራ ሦስት ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት 180 ቢሊየን ብር ዋጋ ያላቸው 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርቶች ማገበያየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img