Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአፋር ክልል ሕወሓት እያካሄደ ነው ያለውን ‹‹የዘር ጭፍጨፋ›› እንዲያቆም አሳሰበ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 9 2014 ― የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሕወሓት የአፋር ሕዝብ ላይ በድጋሚ እያካሄደ ነው ያለውን ‹‹የዘር ጭፍጨፋ›› በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳስቧል፡፡

ክልሉ በኮሚኒኬሽን ቢሮው በኩል ባወጣው መግለጫ፣ ሕወሃት በኪልበቲ ረሱ ዞን ሁለት በአብአላ በኩል ከታኅሣሥ 10፣ 2014 ጀምሮ ‹‹በከፈተው አዲስ ግንባር›› በተከታታይ እየተኮሰ በከባድ መሳሪያ ንፁሐን ዜጎችን መጨፍጨፉን ቀጥሏል ሲል ክስ አቅርቧል፡፡

እንደ ክልሉ ከሆነ ሕወሓት በሚሰነዝረው ‹‹በከባድ መሳሪያ የታገዘ ድብደባ›› በርካቶች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን፣ መቁሰላቸውን እንዲሁም በበርካታ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ‹‹በጥቃቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስደት›› ተዳርገዋል፡፡

የክልሉ መንግስት አክሎም ‹‹የትግራይን ህዝብ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር ለማናከስ ቆርጦ የተነሳ›› ነው ያለው ሕወሓት ‹‹ጎረቤታሞች በሰላም ውሎ እንዳያድሩ›› ትልቅ ጥረት በማድረግ ላይ ስለሆነ የትግራይ ሕዝብ ይህን ‹‹እብደት›› ሲል የጠራውን ድርጊት እንዲያወግዝ ጠይቋል፡፡

የአፋር ክልል በመግለጫው ሕወሓት ቅዳሜ ጥር 7 እና ትላንት እሑድ ጥር 8፣ 2014 ‹‹በተለየ መልኩ ተደራጅቶ በመምጣት›› ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ በርካታ ንፁሀን ላይ ጉዳት በማድረስ፣ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እና የግለሰብ የንግድ ተቋማት እንዲሁም መኖሪያ ቤቶችን ማውደሙንም ጠቅሷል፡፡

የክልሉ መንግስት በመግለጫው ማሳረጊያ፣ የዓለም ኅብረተሰብ ሕወሓት ‹‹በድጋሚ በንፁሀን አፋሮች ላይ እያደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እና ሰላም ወዳዱ የአፋር ህዝብ በቤቱ በሰላም እንዳያድር እያደረገ ያለውን የሽብር ተግባር ሊያወግዝ እና ቡድኑ እያደረገ ያለውን ዳግም ወረራ በአስቸኳይ ማቆም ይገባዋል›› ብሏል፡፡

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ላሰማው ክስ ከሕወሓት በኩል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰአት ድረስ ያለው ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img