Sunday, September 22, 2024
spot_img

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለድንበር መዘጋት ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለማበጀት እየሠሩ እንደሚገኙ ተገለጸ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ጥር 7፣ 2014 ― ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለድንበር መዘጋት ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለማበጀት እየሰሩ እንደሚገኙ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደር ጀማል አል ሼክ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር ጀማል አል ሼክ ሱዳን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለረዥም ዘመናት የዘለቀ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውና ይህ ግንኙነት በዘላቂነት ማስቀጠል የሱዳን ህዝብና መንግስት ጥልቅ ፍላጎት እንደሆነ መናገራቸውን የአል ዐይን ዘገባ ያመለክታል፡፡

የኢትዮ ሱዳን ድንበር ጉዳይ አሁንም በሂደት ላይ ያለ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ሁለቱም ሀገራት የድንበሩ መዘጋት ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ለማበጀት እየሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

አምባሳደር ጀማል አል ሼክ፤ አሁን በሱዳን ቁጥጥር ስር ስለሚገኘውና የይገባኛል ጥያቄና ክርክር እየተነሳበት ስላለው ስፍራን በተመለከተ ሱዳን ያላትን አቋም ምን እንደሚመስል ከአል ዐይን ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።

‹‹አሁን ክርክር እያስነሳ ያለው መሬት ሱዳን የኔ ነው ብላ ታምናለች›› ያሉት አምባሳደር ጀማል፤ ሱዳን ጉዳዩ ከፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ውጭ በሌሎች አማራጮች ይፈታል ብላ እንደማታምንም ተናግረዋል፡

‹‹የሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ለሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት እንቅፋት ሊሆን አይችልም›› የሚሉት አምባሳደር ጀማል፤ ሱዳን ጉዳዩን በዲፕሎማሲ እና ፖለቲካዊ ውይይት ለመፍታት ፍላጎት እንዳላት ገልፀዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ በሁለቱም ሀገራት በኩል የድንበሩን ጉዳይ የሚፈታ አካል አለ፣ ጉዳዩ በዚያ መልክ ከተፈታ በኋላ ጉዳዩ ለሁለቱ ሀገራ የኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚያዊ ግንኑነቶችን እንደ አዲስ ለማደስ ያስችላል። ‹‹አሁን ላይ የሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የተረጋጋ ነው›› ያሉት አምባሳደር ጀማል አል ሼክ፤ በቅርቡ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር አዋሳኝ ክልሎች ውጤታማ የሰላም እና ልማት ጉባኤ ማካሄዳቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የሱዳን መንግሥት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳባቸውን የአል ፋሽቃ አካባቢን የተቆጣጠረው ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ወደ ተቀሰቀሰው ግጭት መሰማራቱን ተከትሎ ነበር።

የድንበሩን ጉዳይ በተመለከተ መንግሥት በተደጋጋሚ በሰላማዊ መንገድ በውይይት ይፈታ ዘንድ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጿል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img