Sunday, September 22, 2024
spot_img

መንግሥት በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ ለዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ጠባቂ ቦርድ የቅሬታ ማመልከቻ አስገባ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ጥር 6፣ 2014 ― የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ ያለውን ቅሬታ የሚገልጽ ደብዳቤ ለድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ቦርድ አስገብቷል፡፡

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ የመንግስት ደብዳቤ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በሥነ ምግባር ጥሰት እንዲጠየቁለት የሚጠይቅ ነው፡፡   

መንግስት ለዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ጠባቂ ቦርድ በላከው የቅሬታ ማመልከቻ፣ በዳይሬክተሩ የተነሳ የድርጅቱ የገለልተኝነት መርህ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን አመልክቷል፡፡

አያይዞም ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት እንዲመሩ ያጨቻቸው ቢሆንም፣ ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት ከወሰደ ግለሰብ የሚጠበቅ ሙያዊ ገለልተኝነት እንዳላሳዩ አስፍሯል፡፡

መንግስት በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ በቅሬታ ከዘረዘራቸው ሙያዊ የሥነ ምግባር ጥሰት መካከል ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ጣልቃ መግባታቸውን፣ በአሸባሪነት ለተፈረጀው ሕወሓት ድጋፍ መስጠት መቀጠላቸውን እና አባል መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡  

ለዓለም ጤና ድርጅት የበላይ ጠባቂ ቦርድ በተላከው የቅሬታ ደብዳቤ ላይ ዶክተር ቴድሮስ የሕወሓት ወታደራዊ ድሎችን ሲያስመዘግብ ደስታቸውን እንደሚገልጹ የጠቀሰ ሲሆን፤ ሰብአዊ ቀውሶች ሲፈጠሩም በተለየ ለአንድ ቦታ ብቻ እንደሚያደሉ በመክሰስ፣ ይህን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ መመልከት እንደሚቻል ጠቁሟል፡፡

የትግራይ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ከዚህ ቀደም የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአንድ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርን ‹‹ወንጀለኛ ነው›› ሲሉ ተናግረው ነበር።

ፊልድ ማርሻሉ ወንጀለኛ ነው ለማለታቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ዶክተር ቴድሮስ የዓለም አቀፍ ተልዕኮ ዕድላቸውን ተጠቅመው የሕወሓት ቡድንን ለመርዳት ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በቅርቡ ባስተላለፉት ቪድዮ ላይ ድርጅታቸው በትግራይና ሌሎች በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ያቀረቡት ርዳታ እንደነበረና ይህ ርዳታ ወደ አፋርና አማራ አካባቢዎች ማድረስ ቢፈቀድላቸውም ወደ ትግራይ መላክ እንደተከለከሉ ገልጸው ነበር፡፡

በሌላ ንግግራቸው በዓለም ላይ በትግራይ እየደረሰ ያለውን ዓይነት መዓት የትም ዓለም ማየት አይቻልም ያሉት ዶክተር ቴድሮስ፣ ትግራይ ‹ገሐነም ሆናለች› ብለው ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img