አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥር 5፣ 2014 ― ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምክከር መድረክ ለሚሳተፉ አካላት ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጧል፡፡
ፓርቲው በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ላይ በምክክሩ የሚሳተፉ አካላት ‹‹የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት ማስቀጠል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል›› እና ‹‹በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ›› የሚቀበሉ መሆን አለባቸው ብሏል፡፡
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ባልደራስ ለአገራዊ ምክክሩ ይረዳሉ ያላቸውን ምክረ ሃሳቦችም በዛሬ መግለጫው ላይ አቅርቧል። ፓርቲው ያቀረበው የመጀመሪያው ምክረ ሃሳብ፤ ምክክሩን ሁሉም ባለድርሻዎች በባለቤትነት የሚመሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚጠይቅ ሲሆን፣ የምክከር ሂደቱም ‹‹ግልጽ፣ ተአማኒ እና ከገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ነጻ›› እንዲሆን ብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የምክክር ሂደቱን ግልጽነት ለመፍጠር ‹‹ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በታዛቢነት እንዲጋበዙ ጠይቋል፡፡
ሌሎች ጉዳዮች በተነሱበት በዛሬው የባልደራስ መግለጫ፣ መንግስት ምዕራፍ አንድን አጠናቅቄያለሁ ስላለበት ከሕወሓት ጋር ስለነበረው ጦርነት ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ ወቅት ፓርቲው መንግስት ምዕራፍ አንድ ያለውን ዘመቻ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሳያረጋግጥ ማቆሙ ‹‹ትልቅ አደጋ ያዘለ ነው›› ሲል ስጋቱን ገልጿል። አያይዞም ህወሓት አሁንም የሀገሪቱን አንድነት ሊፈታተን በሚችል ወታደራዊ ቁመና ላይ ይገኛል ያለው ባልደራስ፤ መንግስት ዘመቻውን ያቆመበትን ምክንያት በተመለከተ በቂ ምላሽ አልሰጠም ሲል ተችቷል።
በሌላ በኩል የባልደራስ ሊቀመንበር አቶ እስክክድር ነጋን ጨምሮ በተፈቱበት ዕለት በተመሳሳይ መልኩ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ስድስት ህወሓት አመራሮች ጉዳይ በመድረኩ ተንስቷል፡፡ ባልደራስ የኢትዮጵያ መንግስት የእነዚህን የህወሓት አመራሮች ክስ አቋርጦ እንዲፈቱ መወሰኑን ‹‹የህግ የበላይነትን የጣሰ ውሳኔ›› ሲል ገልጾታል፡፡ ፓርቲው ክስ የተቋረጠላቸውን ግለሰቦች ‹‹የህወሓት የፖለቲካ እነ የጦርነቱ ዋነኛ ቀያሾች›› እንደሆኑ ገልጧል፡፡