Thursday, November 21, 2024
spot_img

መንግሥት ሕወሓት ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይቀርብ እንቅፋት ሆኗል ሲል ከሰሰ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ጥር 5 2014 ― የፌዴራል መንግሥት ሕወሓት ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይቀርብ እንቅፋት ሆኗል ሲል በዛሬው እለት ክሱን አሰምቷል፡፡

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ባወጣው መግለጫ፣ መንግስት ለትግራይ ህዝብ ባለው ‹‹ውግንናና የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ያለ ምንም መስተጓጐል በአፋር ክልል በአብአላ በኩል በቀጥታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲጓጓዝ ባስቀመጠው አቅጣጫ›› እንዲሁም ‹‹የአፋር ክልል መንግሥትና ህዝብ ለትግራይ ክልል ባላቸው አጋርነት›› ከሐምሌ 5፣ 2013 ጀምሮ በ1 ሺሕ 10 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀርብ ማድረጉን አስታውሷል፡፡

ነገር ግን የህወሃት ቡድን ‹‹የትግራይን ህዝብ በስም ለመነገጃነት ከማዋል ውጪ ቆሜለታለሁ ብሎ ለሚሰብከው ህዝብ እንኳ ሰብዓዊነት የማይሰማው በመሆኑ›› ዕርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ የገቡት 1 ሺሕ 10 ተሽከርካሪዎች ተመልሰው ዕርዳታ ጭነው ወደ ክልሉ እንዲመለሱ በማድረግ ፋንታ አማራና አፋር ክልልን ሲወር የሠራዊቱ ማጓጓዣ አድርጐ ተጠቅሞባቸዋል ብሏል፡፡

መግለጫው በተጨማሪም ቡድኑ እንደ ኮምቦልቻና ሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ የመንግሥትና የግል መጋዘኖች ዘርፎታል ያለውን ስንዴና ሌሎች ምግብና ምግብ – ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶች ‹‹በትግራይ ክልል በሚገኙ መጋዘኖች ካከማቸ በኋላ›› ወደ ትግራይ ክልል ርዳታ ማስገቢያ በሆነው በአብዓላ መስመር ‹‹ወረራ በማካሄድና የከባድ መሣሪያ ተኩስ በመክፈት መስመሩ እንዲዘጋ በማድረግ›› ከታኅሣሥ 6፣ 2014 ጀምሮ ርዳታ እንዳይቀርብ አስተጓጉሏል ሲል ውንጀላ አቅርቧል፡፡

አክሎም ሕወሓት ይህን ቢፈጽምም እንደ ዓለም ጤና ድርጅት አይነት ‹‹ለሁሉም ሰው በእኩል ቆመናል የሚሉ አለም አቀፍ ተቋማት›› ቡድኑ የአማራና አፋር ክልሎችን በወረረበት ወቅት ሆስፒታሎችንና የጤና ጣቢያዎችን ሲዘርፍና ሲያወድም ንፁሃንን ሲደፍርና ሲገድል የሽብር ቡድኑን ድርጊት ሲያወግዙ አልተደመጡም ሲል በተቋማቱ ላይ ቅሬታ አቅርቧል፡፡

እነዚህ ተቋማት መንግስት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይገባ እያደረገ ነው በሚል ሕወሓት ‹‹የሚያሰማውን ፕሮፖጋንዳ ተቀብለው እያስተጋቡት ይገኛል›› ያለው መግለጫው፣ ይህ በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ገልጧል፡፡

መንግስት በመግለጫው ምንም እንኳ ቀደም ብለው ዕርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ገብተው ያልተመለሱ 1 ሺሕ 10 ከባድ ተሽከርካሪዎች በክልሉ መኖራቸውን እያወቀ በዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለቤትነት ሥር ያሉ 118 ከባድ ተሽከርካሪዎች በሙሉ አቅማቸው የዕርዳታ ማጓጓዝ ሥራ እንዲሰሩ መፍቀዱን የገለጸ ሲሆን፣ ዕርዳታውን ለሚያጓጉዙ ሾፌሮችም ሙሉ የደህንነት ዋስትና እንዲያገኙ አድርጌያለሁ ብሏል፡፡  

ከዚህም በላይ በቀጣይነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትና የዕርዳታ አቅርቦቱ ያለ እንቅፋት እንዲከናወን ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት እንደተጠበቀ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

መንግስት በመግለጫው ማሳረጊያም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብና አጋር አካላት የህወሃትን ቡድን ‹‹እኩይ›› ያለውን ተግባርና ‹‹የእርዳታ እንቅስቃሴ አደናቃፊነት እንዲኮንኑ›› በማሳሰብ፣ እንደ ወትሮው የዕርዳታ አቅርቦቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ የበኩሉን ሁሉ እንደሚወጣ ገልጧል፡፡

 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img