Thursday, October 17, 2024
spot_img

አምባሳደር ፌልትማን ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በመንግሥት ጥሪ እንደነበር ተገለጸ

  • ጠ/ሚ ዐቢይ እና ባይደን ላደረጉት የስልክ ውይይትተነሳሽነቱን የወሰዱት ባይደን ናቸው

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጥር 4፣ 2014 ― የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በመንግሥት ጥሪ መሆኑን በዋይት ሐውስ ድረ ገጽ በተነበበ ቃለ-ምልልስ ሥማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣን ገልጸዋል፡፡

ልዩ መልእክተኛው ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸው የተነገረው ባለፋው ሳምንት ሐሙስ ታኅሣሥ 28፣ 2014 የነበረ ሲሆን፣ ስለ ኢትዮጵያ ቆይታቸው ዝርዝር መረጃዎች በወቅቱ አልወጡም ነበር፡፡ ነገር ግን የልዩ መልእክተኛውን የኢትዮጵያ ጉብኝት አስመልክቶ በወጡ ዘገባዎች አሜሪካ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተገናኘ በቀጣይ አዎንታዊ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል ተስፋ ማድረጓ ተነግሮ ነበር፡፡

ቆይቶ መግለጫ ያወጣው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ቀንድ ልዑኩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መወያየታቸውን አመልክቷል፡፡ ሆኖም ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የአምባሳደሩን ቆይታ በተመለከተ የወጣ ይፋዊ መረጃ የለም፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ በተያዘው ወር መጨረሻ ኃላፊነታቸውን የሚለቁት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን በመተካት የተሾሙት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ መቼ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ለመጓዝ እንዳሰቡ አለመታወቁ ተነግሯል፡፡ በዋይት ሐውስ ድረ ገጽ በተነበበውና ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለስልጣን እንዳመለከቱት የልዩ መልዕክተኛውን የጉብኝት ቀን በተመለከተ የተወሰነ ቀን አለመኖሩን ገልጸው፣ ‹‹ነገር ግን ረዥም ጊዜ እንደማይሆን እንጠብቃለን›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሰኞ ጥር 1፣ 2014 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በስልክ ውይይት አድርገዋል፡፡ ይህ የስልክ ውይይት በፕሬዝዳንት ባይደን ተነሳሽነት የተደረገ ስለመሆኑም ተገልጧል፡፡

ድምጸቱ ኮስተር ያለና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር በተባለው በዚሁ የሁለቱ መሪዎች የስልክ ውይይት ላይ ኢትዮጵያና አሜሪካ በጋራ መከባበርን መሰረት በማድረግ ገንቢ ግንኙነት በማድረግ ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በኩል ተነግሯል፡፡

ዋይት ሐውስ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ባይደን በመላው ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በሚሻሻልበት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ሰዎችና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ገልጿል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img