Sunday, September 22, 2024
spot_img

መንግሥት የአየር ድብደባ ማካሄዱን አቁሞ ሰላማዊ ድርድር እንጂምር ጆ ባይደን ጠየቁ

  • ጠ/ሚ ዐቢይ እና ጆ ባደን ያደረጉት የስልክ ውይይት ድምጸቱ ኮስተር ያለና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ጥር 3 2014 ― የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የኢትዮጵያ መንግሥት የአየር ድብደባ ማካሄዱን አቁሞ ሰላማዊ ድርድር እንዲጀምር የጠየቁት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ ወቅት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባይደን በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ወቅታዊ ጉዳዮች፣ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በትላንትናው እለት ግልጽ ውይይት ማድረጋቸው በሁለቱም አገራት በኩል ይፋ ተደርጓል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የጆ ባይደንን የስልክ ውይይት ያደመጡ የዋይት ሃውስ ሰዎች የሁለቱ መሪዎች የስልክ ንግግር ድምጸት ኮስተር ያለና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን ቀድመው ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያና አሜሪካ በጋራ መከባበርን መሰረት በማድረግ ገንቢ ግንኙነት በማድረግ ትብብራቸውን ለማጠናከር ከባይደን ጋር መስማማታቸውን አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽሕፈት ቤታቸው በኩል በወጣው መግለጫ ላይ ‹‹ኢትዮጵያ በሰሜናዊ ክፍሏ ስላካሄደችው ሕግ የማስከበር ዘመቻ›› ያለበት ሁኔታ መግለጻቸውን ጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ስለ ሰብአዊ እርዳታ፣ ሰብአዊ መብቶችን እና በቅርቡ ነጻ በወጡ አካባቢዎች መልሶ ግንባታን በሚመለከት የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት አንስተው ማብራራታቸውን ገልጿል።

ዋይት ሐውስ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በሁለቱ መሪዎች መካከል በአገሪቱ እየተካሄደ ስለሚገኘው ጦርነት እንዲሁም ሰላምና እርቅ ለማውረድ ስላሉ ዕድሎች ውይይት መደረጉን አመልክቷል፡፡

ፕሬዝዳንት ባይደን በቅርቡ በኢትዮጵያ ስለተፈቱ የፖለቲካ አስረኞች ጉዳይ አንስተው በጎ አስተያየት መሰንዘራቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ በጦርነቱም ድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም ማድረግን በተመለከተ ተነጋግረዋል ሲል ዋይት ሐውስ አስታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ባይደን በመላው ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በሚሻሻልበት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ሰዎችና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውም ተገልጿል።

በስልክ ቆይታው ወቅት ፕሬዝዳንት ባይደን በቅርቡ የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶችን ጨምሮ የቀጠለው ግጭት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸው እንዳሳሰባቸው በመጥቀስ፣ አሜሪካ ከአፍሪካ ኅብረትና አካባቢያዊ አጋሮች ጋር በመሆን ግጭቱ በሰላም እንዲያበቃ ድጋፍ እንደምታደርግ መናገራቸውን ጽሕፈት ቤታቸው ገልጧል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት እና አሜሪካ የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ ግንኙነታቸው መሻከሩ ይታወቃል። በጦርነቱ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ሲያወጣ የሰነበተው የአሜሪካ መንግስት፣ በኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናት ላይ የቪዛ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያንም ከአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት ሰርዟል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img