Sunday, November 24, 2024
spot_img

የኤርትራ ጦር በሽራሮ አቅራቢያ አዲስ ጥቃት መክፈቱን የሕወሓት ቃል አቀባይ ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጥር 2፣ 2014 ― የጎረቤት ኤርትራ ጦር በሽራሮ አቅራቢያ አዲስ ጥቃት መክፈቱን የሕወሓት ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ባሰፈሩት የትዊተር ማስታወሻ፣ የኤርትራ ጦር በሰሜን ምእራብ ትግራይ በሚገኘው ስገም ኮፎሎ ጥቃቱን ከፍቷል ያሉት ከትላንት በስትያ ታኅሣሥ 30፣ 2014 ነው፡፡

ጥቃቱን በተመለከተ ሰንዝሮታል ከተባለው የኤርትራ መንግስትም ሆነ ከሌላ ወገን የተሰጠ ማረጋገጫ የለም፡፡

በሌላ በኩል በዚያው በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ባለፈው ዐርብ 56 ሰዎች በአየር ጥቃት ተገድለዋል መባሉን ተከትሎ የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በአካባቢ የሚያደርጉትን የረድኤት ሥራ ማቋረጣቸውን ተገልጧል፡፡

ሬውተርስ እና አጃንስ ፈራንስ ፕረስ ይዘዋቸው በወጡ ዘገባዎች ባለፈው ዓርብ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ካምፕ ላይ በተፈጸመው የአየር ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የእርዳታ ድርጅቶች በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሥራ ማቋረጣቸውን የተባበሩት መንግሥት አስቸኳይ ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ጠቅሰው ዘግበዋል።

የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው በትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ በምትገኘውና የኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ባለች ደደቢት ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት መሆኑንም የእርዳታ ሠራተኞቹ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡

ኦቻ ስለ እርዳታ ሥራው መቋረጥ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም በሰጠው ምላሽ ‹‹የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ አጋሮች በአካባቢው ባለው የድሮን ጥቃት ስጋት እንቅስቃሴያቸውን ለጊዜው አቋርጠዋል›› ማለቱን ሬውተርስ በዘገባው አመልክቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img