አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 28፣ 2014 ― ቻይና በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ልትሾም መሆኑን ያስታወቁት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ናቸው።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ይህንኑ በኬንያ ጉብኝታቸው ወቅት ተናግረዋል።
ቻይና የምትሾመው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በቀጠናው ያሉ ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን የፀጥታ እና ደህንነት ስጋቶችን ለመቀልበስ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያሉ ሀገራ በሀገራቸው ውስጥ ያሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ተወያይተው ሊፈቱ ይገባል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በቀጠናው ሰላማዊ ድርድሮች እንዲካሄዱም ቻይና ሁኔታዎችን የሚያመቻች ተጠሪነቱ ለሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሆነ ልዩ መልዕክተኛ በቅርቡ ተልካለች ብለዋል።
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሰሞኑ በሌላኛዋ የምሥራቅ አፍሪካ አገር ኤርትራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል።
በምሥራቅ አፍሪካ ከቻይና ቀድሞ አሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ መሾሟ የሚታወቅ ነው።