አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 27፣ 2014 ― ያለፉትን ዘጠኝ ወራት የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ሆነው ያገለገሉት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን ከኃላፊነታቸው ወርደው፣ በሌላ ሊተኩ እንደሆነ ተዘግቧል።
ሬውተርስ የዜና ወኪል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በተያዘው ወር ኃላፊነታቸውን የሚለቁት ፌልትማን የሚተኩት አብዛኛውን ጊዜያቸው በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ባሳለፉት አንጋፋው ዴቪድ ሳተርፊልድ ነው።
በአዲስ ባለሥልጣን ይተካሉ የተባሉት ፌልትማን፣ ነገ ሐሙስ ታኅሣሥ 28 ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያቀኑ መነገሩ አይዘነጋም።
ሬውተርስ የ62 ዓመቱ ፌልትማን ቀድሞም በምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛነት ሲመደቡ፣ ከአንድ ዓመት ላነሰ ጊዜ ብቻ የማገልገል ፍላጎት እንደነበራቸው በዘገባው አመልክቷል።
ጄፍሪ ፌልትማን ዘጠኝ ወራት በዘለቀ የቀጠናው ኃላፊነት ጊዜያቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የሆኑት ኢትዮጵያ እና ሱዳን በችግሮች የተወጠሩበት የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ ዐይነተኛ መፍትሔ አላገኙም።
ፌልትማንን የሚተኩት አንጋፋው ሰው ሳተርፊልድ፣ በቱርክ፣ ሳዑዲ አረብያ፣ ሶርዬ፣ ሊባኖስ እና ቱኒዝያ አገልግለዋል።