Friday, November 22, 2024
spot_img

ሂዩማን ራይትስ ዎች ከሳዑዲ የተመለሱ የትግራይ ተወላጆች በደል ተፈጽሞባቸዋል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 27 2014 ― ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ በቅርቡ ከሳዑዲ ዐረቢያ የተባረሩ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ከሕግ ውጪ በደል ተፈጽሞባቸዋል ሲል አስታውቋል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች በድረ ገጹ ባስነበበው መረጃ ከሳዑዲ የተመለሱት የትግራይ ተወላጆች እስር፣ መንገላታት እና የደረሱበት እንዳይታወቅ መደረጋቸውን የገለጸ ሲሆን፣ የሳዑዲ መንግሥት ስደተኞቹን የሚይዝበትን አስከፊ ሁኔታና ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን እንዲያቆም ጠይቋል።

የመብት ተሟጋቹ ድርጅት በተለያዩ ጊዜ ከሳዑዲ ዐረቢያ የሚባረሩ የትግራይ ተወላጆችን የመንግሥት ባለስልጣናት አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኙ የመቀበያ ጣቢያዎች እንደሚያስገቧቸውና አንደንዶቹም ከሕግ ውጪ እንዲቆዩ እንደሚደረግ ነው ያመለከተው፡፡

ጨምሮም ከተመላሾቹ መካከል ወደ ትግራይ በመጓዝ ላይ የነበሩ ሰዎች በመንገድ ላይ ወይም አፋር ክልል ውስጥ ተይዘው እዚያው ክልል ውስጥና በደቡብ ኢትዮጵያ የማቆያ ቦታዎች ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን ገልጿል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ላወጣው መረጃ ከሳዑዲ ተመላሽ የሆኑ 23 የትራይ ተወላጆችን ማናገሩን በመጥቀስ፣ እነዚህ ተመላሾች ለወራት በአዲስ አበባ፣ በአፋር፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ሾኔ፣ በኦሮሚያ ጂማ ውስጥ በሚገኙ የማቆያ ቦታዎች ተይዘው መቆየታቸውንም ገልጿል።

የሂዩማን ራይትስ ዎች የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ተመራማሪ የሆኑት ናዲያ ሐርድማን በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ አስከፊ በደሎች የገጠማቸው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በማቆያ ማዕከላት ውስጥ እንዲያዙ መደረጋቸውን በመጥቀስ፣ ተመላሾቹ የነበሩባት ሳዑዲ ዐረቢያ ከለላ መስጠት አለባት ያሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ‹‹ከሕግ ውጪ በእስር ላይ ይገኛሉ›› ያሏቸውን ግለሰቦች መልቀቅ እንዳለባት ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በአስከፊ ችግር ውስጥና በእስር ላይ የሚገኙ 40 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው የመመለስ ሥራ መስራቱ ይታወቃል፡፡ እንደ

ሂዩማን ራይትስ ዎች ከሆነ ከፈረንጆቹ ኅዳር 2020 እስከ ሰኔ 2021 ድረስ ከሳዑዲ ከተመለሱት ኢትዮጵያውያን መካከል 40 በመቶው የትግራይ ተወላጆች ናቸው።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ላወጣው መረጃ ምላሽ እንዲሰጡበት ለአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ዋሽንግተን ለሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ፣ ለሳዑዲ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት እና ለሳዑዲ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር በደብዳቤ ብጠይቅም ምላሽ አላገኘሁም ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img