Sunday, September 22, 2024
spot_img

በመንግሥት ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ደቡብ አፍሪካዊ አክቲቪስት በሀገሩ የፀረ መጤዎች እንቅስቃሴ መሪ ነው ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 26 2014 ― በመንግሥት ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ደቡብ አፍሪካዊ አክቲቪስት ሎንታታ ላክስ በሀገሩ የፀረ መጤዎች እንቅስቃሴ መሪ መሆኑ ተነግሯል፡፡

አክቲቪስቱ ሎንታታ ላክስ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት ባሉ ቀናት ለፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ባስተላለፈው የቪድዮ መልእክት እና ኢትዮጵያ ከደረሰ በኋላም ‹አፍሪካውያን ከሀገራችን ደቡብ አፍሪካ ለቀው ይውጡልን› የሚል ይዘት ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡

ሉንታታ ባለፈው ሳምንት ታኅሣሥ 22፣ 2014 በግል የዩትዩብ ገጹ ባሰራጨው ቪድዮ ‹‹2022 ደቡብ አፍሪካን የምናስመልስበት ዓመት ነው›› የሚል ርእስ በሰጠው ንግግሩ፣ ሕገ ወጥ ባላቸውና በተለያዩ ነገሮች ዝርፊያ እና ወንጀል ተሰማርተዋል ላላቸው የውጭ አገራት ዜጎች ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ ይደመጣል፡፡

አክቲቪስቱ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ባሰራጨው ሌላ ቪድዮ ደግሞ እርሱ የፓርላማ ፕሬዝዳንት ነኝ በሚልበት የሱዌቶ ግዛት የውጭ አገራት ዜጎች በተለምዶ ‹‹ስፓዛ›› የሚባሉ ሱቆችን መክፈት እንደማይችሉ በማስጠንቀቁ መጤ ጠልነትን የሚያነሳሳ እና ጥላቻን የሚዘራ ነው በሚል መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡

ግለሰቡ ዛሬ ጧት በተመሳሳይ በጻፈው የኢንስታግራም መልእክት አፍሪካውያንን ‹ወደ ሀገራችሁ ተመለሱ› የሚል ያሰፈረ ሲሆን፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይደረጋል ያለውን ‹‹ሕገ ወጥ›› ስደት ‹‹የኒዮ ኮሎኒያሊስቶች ሴራ ነው›› ሲል ገልጾታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ታኅሣሥ 22፣ 2014 ባሰፈረው የትዊተር ማስታወሻ ላይ ህገ ወጥ ለሚላቸው ስደተኞች ደቡብ አፍሪካን ለቀው እንዲወጡ ‹‹የመጨረሻ›› ማሳሰብያ ጽፏል፡፡

የሎንታታ ላክስ አገር ደቡብ አፍሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን በስደት ተጠግተው የሚኖሩባት መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን፣ በቅርብ ዓመታት በተደጋጋሚ በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካውያን ላይ ጥቃት ሲደርስ ሎንታታ ላክስ እና ሌሎች ግብረ አበሮቹ ተባባሪ እንደነበሩ ይነገራል፡፡

ሎንታታ ያለበት ከጆሃንስበርግ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ሱዌቶ በደቡብ አፍሪካ ስደተኛ ጠል እንቅስቃሴዎች ይበልጥ የሚቀጣጠሉበት ከተማ መሆኑም ይነገራል፡፡

በመንግስት ብዙኃን መገናኛዎች ትላንት በሰፈሩ መረጃዎች ሎንታታ በደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያውያን ጎን በመሆን ‹ኖ ሞር› በተሰኘው ንቅናቄ ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱ ሲገለጽ፣ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለመጎብኘት መምጣቱም ሠፍሯል፡፡

አክቲቪስቱ ትላንት አዲስ አበባ ሲገባ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት አቶ ነብዩ ባዬ እና ሌሎች የመንግስት ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ብዙኃን መገናኛዎች የዜና ሽፋን ሰጥተውታል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በተደጋጋሚ በሚከሰተው የመጤ ጠሎች እንቅስቃሴ በርካቶች የጥቃት፣ የዘረፋ እንዲሁም የግድያ ሰለባ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img