Saturday, October 12, 2024
spot_img

ከሰማንያ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዐረቢያ በእስር ላይ መሆናቸው ተጠቆመ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 25፣ 2014 ― ከሰማንያ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ዐረቢያ በእስር ላይ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ገብረ ማርያም ይህን የጠቆሙት፣ ታኅሣሥ 21፣ 2014 በተካሄደው ‹‹ኢትዮጵያ ቤቴ›› የተሰኘ ስደተኞችን ወደ አገር ቤት የመመለስ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ መንግሥት ከወራት በፊት በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር ላይ የነበሩ 40 ሺሕ ያህል ኢትዮጵያዊ ስደተኞችን በ15 ቀናት ውስጥ ወደ አገር እንደመለሰ አስታውሰው፣ አሁንም ‹‹ሳዑዲ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ለይቶ የማሰር ሁኔታ ይታያል›› ማለታቸውን የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ 80 ሺሕ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸውና የሌላቸው ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ላይ የሚገኙ መሆናቸውንም በመጥቀስ፣ መንግሥት እነዚህን ዜጎች ወደ አገር ቤት የመመለስ ሥራ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ፣ ከአጋር ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡  

ይሁንና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለተመላሾች ብሎ አገር ውስጥ የተከራያቸው ሰባት የስደተኛ መጠለያዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ከዚህ ቀደም በመጡ ስደተኞች እንደተሞሉ ለጋዜጣው ያስረዱት አቶ መስፍን፣ መጠለያ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ስደተኞች የጦርነት ቀጣና ከነበረው የሰሜኑ ክፍል የመጡ በመሆናቸው ከመጠለያ እንዲወጡ ማድረግ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

አሁን በሳዑዲ በእስር ላይ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያንም ቢሆኑ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሄዱና ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ወደ ቀዬአቸው መመለስ የማይችሉ በመሆናቸው፣ መጠለያዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ዜጎቹን ወደ አገር ቤት የመመለስ ሥራው የመንግሥት ውሳኔን የሚጠይቅ መሆኑን ያስረዱት አቶ መስፍን፣ ሥራው በቅርቡ ይጀመራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አክለዋል፡፡

ከሰሞኑ በተለያዩ የበይነ መረብ ብዙኃን መገናኛዎች በወጡ መረጃዎች በሳዑዲ እስር ቤት እየተሰቃየን እንገኛለን ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን የመንግስት አካል ይድረስልን ሲሉ ጥሪ ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡

በቁጥር በርካታ መሆናቸው የተነገረላቸው እነዚህ እስረኞች በመካከላቸው አቅመ ደካሞችና ሴቶች እንዲሁም ሕፃናት ሳይቀር እንደሚገኙበት ነው የተመላከተው፡፡

አሁን ከ80 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያንን በእስር ቤቶቿ አጉራለች የተባለችው ሳዑዲ ዐረቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን በስደት የሚሄዱባት መሆኗ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img