አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 20፣ 2014 ― የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የአራዳ ሁለተኛ ልዩ ችሎት ባለፈው ሰኞ ታኅሣሥ 18፣ 2014 ፖሊስ መዓዛ መሐመድን በችሎት እንዲያቀርብ በድጋሚ ትዕዛዝ መስጠቱ መነገሩ አይዘነጋም፡፡
ፖሊስ ይህን ትእዛዝ የሰጠው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የማይፈታበትን ምክንያት ቀርቦ እንዲያስረዳ የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለመፈጸሙ ነበር፡፡
ይህንኑ ተከትሎ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትላንት ማክሰኞ ታኅሣሥ 19፣ 2014 ለፍርድ ቤቱ በድጋሚ በጻፈው ደብዳቤ እንደ ቀደመው ጊዜ ሁሉ ተጠርጣሪዋ በኮማንድ ፖስቱ ስር ስለምትገኝ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደማይችል ገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሁለት ሳምንት በፊት በቁጥጥር ስር የዋለችው የሮሃ ቲቪ መስራች መዐዛ መሐመድን ከሕወሓት ተልእኮ በመቀበል ወንጀል ጠርጥሮ እየመረመራት እንደሚገኝ ማሳወቁ አይዘነጋም።
መዐዛ መሐመድ በቁጥጥር ስር ከመዋሏ በፊት ትሠራበት ከነበረው ሮሃ ቲቪ የተሰኘ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን በፊት፣ ዐባይ በተባለ መገናኛ ብዙኃን በምታቀርባቸው ዝግጅቶች በሥፋት ትታወቃለች፡፡