Tuesday, October 8, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን በቀጣይ ወር መገባደጃ ወደ ሥራ ሊመልስ ነው

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 18 2014 ― የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ከጥር 25፣ 2014 ጀምሮ ዳግም ወደ ሥራ ሊመልስ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ተወልደ ገብረ ማርያም ደህንነት የኩባንያው ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፣ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ዳግም ወደ ሥራ ሲመልስም የተለያዩ አገራት የአቪዬሽን ቁጥጥር ተቋማት ለአውሮፕላኑ ዳግም የበረራ ፈቃድ ከሰጡ በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ወደ ሥራ ለመመለስ ከመጨረሻዎቹ አየር መንገዶች ተርታ እንደሚሆን በገባው ቃል መሰረት፣ የዲዛይን ማሻሻያ ሥራውንና ከ20 ወራት በላይ የፈጀውን ጥብቅ የማረጋገጫ ሂደት ሲከታተል እንደቆየና አብራሪዎች፣ ኢንጀሮች፣ የአውሮፕላን ቴክኒሻኖች እና የበረራ ባለሞያዎቹ በአውሮፕላኑ እርግጠኛ እስከሚሆኑ ድረስ መጠበቃቸውንም አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ላየን አየር መንገድ ንብረት የነበሩት ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ተከስክሰው በድምሩ 346 ሰዎች ካለቁ በኋላ አውሮፕላኑ በረራ እንዳያደርግ ለሁለት ዓመታት ታግዶ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በአውሮፕላኖቹ ላይ የምህንድስና ማሻሻያ ተደርጎባቸው የብቃት ፍተሻ መደረጉን ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በረራ እንዲያደርግ ፍቃድ የተሰጠው በብራዚል እና ሰሜን አሜሪካ ነበር፡፡

ከዚያን ጊዜ አንስቶም በአሁኑ ሰዓት በዓለም 34 ያህል አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ዳግም እየተገለገሉበት እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡

በቀጣዩ ጥር ወር አውሮፕላኖቹን ወደ ሥራ እመልሳለሁ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለተጓዦች ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን እንደሚያቀርብ ገልጧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img