አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 18፣ 2014 ― በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ አካባቢ በምትገኘው ደገሌ ጋቲራ ቀበሌ፣ ልዩ ቦታዋ ወዴሳ በተሰኘችው ቦታ 11 አርሶ አደሮች መንግሥት ኦነግ ሸኔ በሚለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚለው ቡድን መገደላቸው ተሠምቷል።
አዲስ ማለዳ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ፣ ግድያው የተፈጸመው ባሳለፍነው ታኅሣሥ 11፣ 2014 ነው።
ታጣቂ ቡድኑ በንጹኃን ላይ ጥቃት ያደረሰው ብሔርንና ማንነትን መሠረት አድርጎ ነው የተባለ ሲሆን፣ ግድያው የተፈጸመው በአርሶ አደሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በሕጻናት ልጆች ጭምር መሆኑ ነው የተነገረው።
ከምሽቱ ስድስት ሰዓት ገደማ ተፈጽሟል በተባለው ግድያ፣ ከመፈጸሙ አንድ ሳምንት በፊት ከ40 በላይ የሚሆኑ ታጣቂዎች አርሶ አደሮቹን ከቤታቸው አስወጥተው ትዕዛዝ እንደሰጧቸው ተገልጿል።
ትዕዛዙም ‹‹መሣሪያ አላችሁ፤ ስለዚህ ለኛ ታስረክቡናላችሁ። ካልሆነ ግን ተመልሰን መጥተን እንገድላኋለን›› የሚል እንደነበር ነው ጋዜጣው ያመላከተው።
ከታጣቂዎቹ ይህ ጥያቄ የቀረበላቸው አርሶ አደሮችም መሣሪያ እንደሌላቸው ለማስረዳት እንደሞከሩ የተመላከተ ሲሆን፣ ታጣቂዎቹም መሣሪያ ከሌላችሁ እያንዳንዳችሁ 200 ሺሕ ብር ሰብስባችሁ ጠብቁን፤ ይህን ካላደረጋችሁ ግን ከሳምንት በኋላ ስንመለስ ‹‹እንገድላችኋለን›› ሲሉ አስፈራርተዋቸው ነበር ነው የተባለው።
በታጣቂ ቡድኑ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሰባቱ አርሶ አደሮች እንደሆኑና ቀሪዎቹ አራቱ ሟቾች ደግሞ የአርሶ አደሮቹ ታዳጊ ልጆች መሆናቸውን ነው መረዳት የተቻለው።
የሟቾቹ ቤተሰቦችም የደረሠባቸውን ለወረዳው አስተዳደር ቢያሳስቡም ‹‹ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ከፈለጋችሁ እናስታጥቃችሁና ተከላከሉ›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ነው መረዳት የተቻለው።
ጉዳዩን በማስመልከት ከኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮም ሆነ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ምላሽ አልተሰጠበትም።