Sunday, October 6, 2024
spot_img

ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ከሚያስቀምጡት መጠባበቂያ ገንዘብ ላይ ብድር መስጠት ጀመሩ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ታኅሣሥ 18 2014 ― ባንኮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚያስቀምጡት መጠባበቂያ ገንዘብ ላይ ለቡና ላኪዎችና አቅራቢዎች ብድር እንዲሰጡ በብሔራዊ ባንክ የተላለፈው መመርያ ከታኅሳስ 13፣ 2014 ጀምሮ መተግበር ጀምሯል፡፡

በኢንዱስትሪው ውስጥ እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ከብሔራዊ ባንክ በተላለፈው መመርያ መሠረት፣ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ከሚያስቀምጡት የአሥር በመቶ መጠባበቂያ ገንዘብ ላይ ሁለት በመቶውን ወጪ በማድረግ ለዚሁ ዘርፍ ብድር እንደተጠቀሙበት ማስታወቁ ነው የተነገረው፡፡

በተለይ የቡና የወጪ ንግድ እንዳይስተጓጎል ባንኮችም የጥሬ ገንዘብ  ችግር እንዳይገጥማቸው ታሳቢ ተደርጎ ተግባራዊ እንዲሆን በተላለፈው መመርያ መሠረት፣ ለቡና ላኪዎችና አቅራቢዎች ብድር ማቅረብ ይችላሉ፡፡

ባንኮቹ ለነዚህ ዘርፎች የሚሰጡት ብድር እያንዳንዱ ባንክ ባለው መጠባበቂያ ገንዘብ ልክ መጠን የሚወሰን ነው፡፡ የተሰጠው ብድር የመመለሻ ጊዜ ገደብ የተቀመጠለት ሲሆን፣ ባንኮቹ ለነዚህ ዘርፎች የሰጡትን ብድር እስከ ነሐሴ 2014 መልሰው ወደ ብሔራዊ ባንክ  ማስገባት ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ በዚህ በብሔራዊ ባንክ ሰሞናዊ ውሳኔ ላይ ካነጋገርኳቸው መካከል አንዱ የሆኑት የኦሮሚያ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ተፈሪ መኮንን፣ ውሳኔው ኃላፊነት የተሞላበትና ወቅቱን የጠበቀ ነው እንዳት አስነብቧል፡፡

ውሳኔው፣ ኢኮኖሚውን በማነቃቃቱ ረገድም ትልቅ ጥቅም አለው ያሉት አቶ ተፈሪ፣ ለዘርፉ የሚሰጠው ብድር ለአገር፣ ለባንክ ደንበኞች፣ ለባንኮች፣ ለገበሬውና በአጠቃላይ በቡና ግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ አካላትን በሙሉ የሚጠቅም መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡትን የመጠባበቂያ የገንዘብ መጠን ማሳደጉ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ለነዚህ ዘርፎች የሚሰጠው ብድርም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ካላቸው የአሥር በመቶ መጠባበቂያ ሁለት በመቶ ያህሉን ነው፡፡

ባንኮች በአሁኑ ወቅት በብሔራዊ ባንክ አዲሱ መመርያ መሠረት ከአምስት ወደ አሥር ያደገውን የመጠባበቂያ ገንዘብ መጠን ሙሉ በሙሉ አስገብተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img