Friday, November 29, 2024
spot_img

በሽብርተኝነት የተጠረጠሩ ግለሰቦች ሕንፃዎችን የተከራዩ ከቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ውል እየፈጸሙ መሆኑ ታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ታኅሣሥ 17፣ 2014 ― ከሕወሓት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ሕንፃዎች ውስጥ ተከራይተው በንግድና በሌሎች ተግባራት የተሰማሩ ሕጋዊ ተከራዮች፣ ቤቶቹን በጊዜያዊነት ከሚያስተዳድረው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ውል እንዲያስሩ እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው የእነ ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ፣ የብርጋዴር ጄኔራል ተክላይ አሸብር፣ የሜጀር ጄኔራል ምግበ ኃይለ፣ የኮሎኔል ፀሐዬ ኪዳኑ፣ የአቶ ዓባይ ፀሐዬና ቤተሰቦቻቸው፣ እንዲሁም በበርካታ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ስም የሚገኙ 25 ሕንፃዎችና የንግድ ተቋማት በጊዜያዊነት በኮርፖሬሽኑ ሥር እንዲተዳደሩ የተደረገ ሲሆን፣ የንብረቶቹ ዕጣ ፈንታ በፍርድ ቤት እስከሚወሰን ድረስ የቤቶቹ ተከራዮች ባሉበት ይዞታና የኪራይ መጠን አዲስ ውል ከኮርፖሬሽኑ ጋር እንዲፈጽሙ ተደርጓል፡፡

በፍርድ ቤት ውሳኔ በኮርፖሬሽኑ ሥር እንዲተዳደሩ አዳዲስ ንብረቶች እንደሚጨመሩ ለሪፖርተር ያስረዱት የኮርፖሬሽኑ ባለሙያ፣ ሕግና ምህንድስናን ጨምሮ በተለያዩ ሙያዎች የተሰማሩ አምስት አባላትን ያቀፈ ኮሚቴ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መመሥረቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ኮሚቴ አማካይነት ንብረቶቹ እንደሚተዳደሩና የኪራይ ገንዘቡም በፍርድ ቤት በሚወሰን መጠን የአስተዳደር ወጪ ተቀንሶ ለእዚሁ ዓላማ በተዘጋጀ የባንክ የሒሳብ እንደሚጠራቀም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ እነዚህ አምስት አባላት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ (አሁን ፍትሕ ሚኒስቴር) አቅራቢነት በሐምሌ ወር 2013 በፍርድ ቤት የዚህ መሰል ሥራ ልምድ ያላቸው መሆናቸው ተመስክሮላቸው የተሾሙ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ሦስት ሥር ብቻ በእነዚህ ሕንፃዎች ውስጥ 142 ቤቶች እንደሚገኙ፣ ምንጩ ባልታወቀ ገንዘብ የተገነቡ፣ አልያም የሚያስገኙት ጥቅምና ሕንፃዎቹ ለሽብር ተግባር እንዳይውሉ ታስቦ ይኼ ውሳኔ መተላለፉ የታወቀ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት ጥፋት ያለባቸው አካላት ንብረቶች ወደ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ባለቤትነት እንደሚተላለፉና ጥፋት የሌለባቸው ደግሞ ለባለንብረቶቹ እንደሚመለሱ በሙያው ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ለማስወሰንም በችሎት ቀርበው ክርክር በማድረግ ላይ የሚገኙ እንዳሉ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ክርክር ላይ የማይገኙ መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

አንዳንዶቹ ባለንብረቶች በተወካዮቻቸው አማካይነት ያከራዩ እንደነበርና የቤት ኪራይም የሚከፈላቸው በእነርሱ ስም በማይገኝ የሒሳብ ቁጥር እንደሆነ በመግለጽ፣ አንዱ የሒሳብ ቁጥር ሲዘጋ እስከ አምስት ድረስ የሒሳብ ቁጥር ያላቸው በመሆኑ በተለያዩ ሐሳቦች የኪራይ ገንዘቦቻቸውን ይሰበስቡ እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ ከሽብር ወንጀል ጋር ግንኙነት ያላቸው ውል ሳይዋዋሉ እንዲወጡና የተከራዩት እንዲታሸጉ፣ እንዲሁም በአስተዳደርና እንደ ጥበቃ ባሉ የሕንፃ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ተነስተው በአዳዲስ ሰዎችና አስተዳዳሪዎች እንዲተኩም ተደርጓል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img