አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 16፣ 2014 ― ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው የሕወሓት ግብአት መሬት ሲፈጸም ብቻ ነው ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በወቅታዊ መግለጫው አሳውቋል።
ፓርቲው በዚሁ መግለጫው በጦርነቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን የገበሩ መሆናቸውን አስታውሶ፣ ለነጻነት የተከፈለ ታላቅ መስዋእትነት ነው ብሎታል።
አያይዞም “ከዳር እስከ ዳር ሆ ብሎ የተመመው ባለሀገር ሊያየው የሚፈልገው ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የሚቻለው” ጠብ ጫሪ ነው ያለው ሕወሓት “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተደምስሶ ግብአተ መሬቱን በመፈጸም” ከዚህ በኋላ በምንም መልኩ የሀገር ስጋት መሆን እንዳይችል ማድረግ ሲቻል ብቻ እንደሆነም ገልጿል።
በሌላ በኩል ኢዜማ ስለ ጦርነት ድርድር እና አገራዊ ምክክር ተደበላልቆ እየወጣ ነው ያለውን መረጃ መንግሥት እንዲያጠራ አሳስቧል።
ፓርቲው የታቀደው አገራዊ ምክክር ከጦርነቱ ጋር ሳይደበላለቅ ለብቻው በጥንቃቄ ታይቶ በችኮላ እና በጥድፊያ እንዳይከናወን ሲል አጽንኦት እንዲሰጠውም ጠይቋል፡፡
ኢዜማ በመግለጫው የትኛውንም ሂደት ስንከትል ‹‹ሕዝባችን የደረሰበትን መከራ›› እና ‹‹እያለፈበት ያለውን ሰቆቃ›› ያገናዘበ እንዲሆን መክሯል፡፡
ዜጎች ከደረሰባቸው መከራ የሚያገግሙበትን ሥራ መሥራት የመንግስት ወቅታዊ ተቀዳሚ ሥራው ሊሆን ይገባል ያለው ፓርቲው፣ ‹‹የገባንበትን መንገድ በገባንበት መንገድ ለመውጣት ከመጣደፍ እንቆጠብ›› ሲል መልእክቱን ሰዷል፡፡
ኢዜማ በተጨማሪም መንግስት ሊያቀቋቁመው በሂደት ላይ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የቀጣይ የምክክሩ የመጀመሪያ አድርጎ በመውሰድ በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መግባባት እንዲደርስ ተገቢውን ጊዜ በመስጠት ረቂቅ አዋጁ ላይ ምክክር እንዲደረግ ምክር ቤቱ እድል እንዲሰጥ ብሏል፡፡ አክሎም ይህን ማድረግ የአገራዊ ምክክሩ ኮሚሽን ከምንግስት ጣልቃ ገብነት ገለልተኛ እንዲሆን ወሳኝ ምእራፍ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡