Friday, November 29, 2024
spot_img

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ብሔራዊ ምክክር አርብቶ አደሮችን እንዲያሳትፍ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 16፣ 2014 ― በኢትዮጵያ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ብሔራዊ ምክክር አርብቶ አደሮችን እንዲያሳትፍ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው፣ ብሔራዊ ውይይቱ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ ያስችል ዘንድ ‹‹በጥንቃቄ እና በገለልተኝነት እንዲመራ›› የጠየቀ ሲሆን፣ በተጨማሪም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች አርብቶ አደሮችን ጨምሮ በራሳቸው ውክልና ኖሯቸው ማንንም ያገለለ ሳይሆን ‹‹በአካታችነት እንዲካሄድ›› ብሎም ገለልተኝነታቸው በተረጋገጡ ሰዎች እንዲመራ መንግስትን አሳስቧል፡፡

በኢትዮጵያ ይካሄዳል ለተባለው ብሔራዊ ምክክር ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ኮሚሽን ለማቋቋም እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ መሠረት ኮሚሽነር ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ጥቆማ የሚቀበለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው ተብሏል።

ጥቆማዎችን የተቀበለው ጽሕፈት ቤቱ ጥቆማዎችን ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማህበራት ከተቀበለ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

በሚስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ በሕዝብ ተወካዮ ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በዚሁ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ጽሕፈት ቤታቸው በኮሚሽነሮች አሰያየም ላይ ያላቸው ሚና ገለልተኝነቱን ጥያቄ ውስጥ ይከትተዋል የሚል ስጋት ከውይይቱ ተሳታፊዎች መነሳቱ ተዘግቧል፡፡

ሰዓታትን በፈጀው በዚህ ውይይት ላይ ኮሚሽነር ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ጥቆማ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀበል የሚል ምክረ ሐሳብ ከበርካታ አስተያየት ሰጪዎች ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን 11 ኮሚሽነሮች እንደሚኖሩት በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ እነዚህ ኮሚሽነሮች ያለ መከሰስ መብት የሚሰጣቸው ይሆናሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img