አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ታኅሣሥ 16፣ 2014 ― በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ቀናት ብቻ ከአስር ሺሕ በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን የጤና ሚኒስቴር እለታዊ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በአራት ቀናት ውስጥ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 10 ሺሕ 569 ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ የ9 ሺሕ 888 ውጤት የተመዘገበው በተከታታይ ባሉት ሦስት ቀናት ነው፡፡
ከነዚህ ቀናት ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው ትላንት ምሽት ነው፡፡ ትላንት ታኅሣሥ 15፣ 2014 የወጣው ሪፖርት ምርመራ ካደረጉ 12 ሺሕ 348 ሰዎች መካከል 4 ሺሕ 573 በቫይረሱ መጠቃታቸው ታውቋል፡፡ በነዚህ ቀናት 16 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሞተዋል፡፡
በኢትዮጵያ በያዝነው ሳምንት በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ፤ አዲሱ የቫይረሱ ዝርያ ኦሚክሮን ገብቶ ከሆነ ለማረጋገጥ የናሙና ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ለብዙኃን መገናኛዎች ተናግረዋል፡፡
ምርምራ እየተደረገበት ነው የተባለው ኦሚክሮን የሚል ሥያሜ ያለው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ልውጥ፣ በዓለማችን ከ100 በላይ አገራት መታየቱ ይፋ ተደርጓል፡፡
ይህ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከጥቂት ሳምንት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ከደቡብ አፍሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ ዝርያው በብዙ የለውጥ ሂደት ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ቀደም ሲል ተይዘው የነበሩ ሰዎች በቫይረሱ የመያዝ ምጥኔን እንደሚጨምር የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡