Friday, November 29, 2024
spot_img

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ ሕወሓት ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች ሕገ ወጥ መታወቂያዎችን ማደሉን ደርሼበታለሁ አለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 15፣ 2014 ― የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ ሕወሓት ተቆጣጥሯቸው በነበሩ አካባቢዎች ሕገ ወጥ መታወቂያዎችን ማደሉን ደርሼበታለሁ ሲል ትላንት ምሽቱን ባወጣው መግለጫው አስታውቋል፡፡

እዙ በመግለጫው ሕወሓት መታወቂያዎቹን ያደለው ባደራጃቸው ሕገ ወጥ መዋቅሮች አማካኝነት፤ የቀደመው አስተዳደር ይጠቀምባቸው የነበሩትን ማኅተሞች በመጠቀምና አዳዲስ ሕገ ወጥ ማኅተሞችን በመቅረጽ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

በመሆኑም በየአካባቢው የተቋቋሙ የመስተዳድር አካላትና የጸጥታ ኃይሎች ሕወሐት ያስቀረጻቸውን ማኅተሞች፣ መታወቂያዎችና ሌሎች ሰነዶች እንዲያመክኑ አዟል።

ተቆጣሯቸው በነበሩ አካባቢዎች ሕገ ወጥ መታወቂያዎችን አድሏል የተባለው ሕወሓት፣ ከትግራይ ክልል ድንበር ተሻግሮ እስከ ሰሜን መድረሱ ተነገሮ የነበረ ቢሆንም፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች ኃይሎች ዳግም አካባቢዎቹን ተቆጣጥረዋል፡፡

በሌላ በኩል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዙ ከሕወሐት ነጻ በወጡት አካባቢዎች አስተዳደርን መልሶ የማቋቋምና መሠረታዊ የኅብረተሰብ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ያለው እንቅስቃሴ ወጥ በሆነ ሁኔታ እየተተገበረ አለመሆኑን እንደገመገመ ገልጿል፡፡

በዚሁ ምክንያት የጸጥታ ችግሮችና የወንጀል ተግባራት ነጻ የወጣውን ማኅበረሰብ እያማረሩት መሆኑን የጠቀሰ ሲሆን፣ ይህ በመሆኑም የአማራ ክልል መንግሥት የየአካባቢውን አስተዳደር በአስቸኳይ በብቁ አመራሮች እንዲያደራጅ፤ መደበኛ የፖሊስ ኃይሎችም የተጠናከረ ሥራ እንዲጀምሩ እንዲያደርግ፣ እነዚህን ለማድረግ ባልተቻለባቸው ቦታዎች የሚንቀሳቀስ የመከላከያ ኃይል፣ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ፣ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ ታዟል ነው ያለው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እዝ በመላው ኢትዮጵያ በጥቅምት ወር መገባደጃ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ ተከትሎ የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img