አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 15፣ 2014 ― በትግራይ ክልልል ተጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል የጠቆሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ናቸው፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህን የጠቆሙት በትላንትናው እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተሰናዳው የአዲስ ወግ መድረክ ላይ ነው፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ በመንግስትና በሕወሓት ኃይሎች መካከል ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ የመጀመሪያ ዙር አዲስ በጀት እየተዘጋጀ መሆኑን የገንዘብ ሚንስትሩ ይፋ አድርገዋል፡፡
በጦርነቱ ሳቢያ የደረሱ ውድመቶችን በዝርዝር የሚያጠና ቡድን ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች በተውጣጡ ሞያተኞች መቋቋሙን እና በቡድኑ ጥናት መነሻነት መንግስት ምላሽ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
እንደ መነሻ የጦርነቱን ተፈናቃዮች መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ ንብረትና መሰረተ ልማቶችን ለመተካት የተለያዩ ማእቀፎች ተዘጋጅተዋል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የመጀመሪያው የድጋፍ ማዕቀፍ 750 ሚሊዮን ዶላር ወይም 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ያህል ተይዞለታል ብለዋል።
ሌላኛው ማእቀፍ የ400 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው ሲሆን፣ በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበር ነው።
በተጨማሪም የ350 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የመልሶ ማቋቋሚያ መርሀ ግብር ደግሞ በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሚከናወን እንደሚሆን ያነሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ በቀጣ ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ለዚሁ መልሶ ማቋቋሚያ ገንዘብ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
በዓመቱ አጋማሽ ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በሚጸድቀው የተጨማሪ በጀትም ዋና ትኩረቱ ይኸው በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋምና የመሰረተ ልማት መልሶ መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።
የተጨማሪ በጀቱ በሚኒስትር መስሪያ ቤታቸው መዘጋጀቱን ያነሱት አቶ አሕመድ፣ መጠኑን ግን አልገለጹም።
አቶ አሕመድ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ሰብአዊ እርዳታዎችን ለማቅረብ 10 ቢሊዮን ብር መውሰዱን የጠቀሱ ሲሆን፣ መልሶ ማቋቋሙ ከሶስት እስከ አምስት ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ነው ፍንጭ የሰጡት፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ መንግስት ኢኮኖሚውን ከጦርነቱ ተፅዕኖ ለማላቀቅ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግም በተመሳሳይ ፍንጭ ሰጥተዋል።