አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 15፣ 2014 ― የአማራ ክልላዊ መንግሥት በስሩ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የክልሉ መንግስት በጥቅምት ወር መገባደጃ የሕወሓት ኃይሎች ድንበር ተሻግረው የተለያዩ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በስሩ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸውን አቋርጠው በጀትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር ለጦርነት እንዲያውሉ መወሰኑ አይዘነጋም፡፡
በትላንትናው እለት መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ 6 ወራትን ያስቆጠረው የሕልውና ያሉት ዘመቻ በመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻው ተጋድሎ ድል መመዝገቡን ገልፀዋል።
ይህንኑ ተከትሎም ክልሉ ጥሎት የነበረው የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ወደ መደበኛ ሁኔታ እንዲመለስ እንደተወሰነ ገልጸዋል፡፡
የመንግስት ተቋማቱ ወደ መደበኛ ሥራቸው ይመለሱ መባሉ የሕልውና ያሉትን ዘመቻ ይተዉታል ማለት አይደለም ያሉት አቶ ግዛቸው፣ ዘመቻውን እየደገፉ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም ተቋማቱ ሥራቸውን ሲጀምሩ በጦርነቱ የተለወጡ ሁኔታዎች በመኖራቸው በመጀመሪያ ከሠራተኞቻቸው ጋር በመወያየት እቅዳቸው መቀየር አለባቸው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ግዛቸው በመግለጫቸው ሕወሓትን ለሀገርና ለህዝብ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ የማክሰም የዘመቻው ግብ ሳይሳካ ትግሉ አይቆምም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የጦርነቱ ግብ ሆኖ የተቀመጠው ህወሓትን ዳግም የኢትዮጵያ እና የአማራ ህዝብ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ማድረስ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ከዚህ አንፃር በርካታ ስራዎች በመቅረታቸው የክልሉ መንግሥት እስከ ድሉ ፍፃሜ ድረስ አበክሮ እንደሚሠራም ገልፀዋል።
በስሩ የሚገኙት የመንግሥት ተቋማት ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ውሳኔ ባሳለፈው የአማራ ክልል፣ ባለፉት ወራት የሕወሓት ኃይሎች ይዘዋቸው በቆዩባቸው አካባቢዎች በርካታ የንብረት ውድመት ያስተናገደ ነው፡፡