Friday, November 29, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ የአጎዋ እድል እገዳ ከፈረንጆቹ ዐዲስ ዓመት ጀምሮ እንዲጸና ተወሰነ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ታኅሣሥ 15 2014 ― የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የአፍሪካ አገራትን ከአፍሪካ ግሮውዝ ኦፖርቹኒቲ አክት (አጎዋ) የቀረጥና ታሪፍ ነፃ መብት መሰረዛቸው ይፋ ተደርጓል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ከአጎዋ ያገደው ከትግራይ ጦርነት ጋር በተገናኘ ሲሆን፣ ማሊ እና ጊኒም በተመሳሳይ ከንግድ መብት ተጠቃሚነቱ የተሰረዙ የአፍሪካ አገራት ሆነዋል፡፡

ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ተፈፅሟል ለተባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ በተጣለው እግድ፣ ለኢትዮጵያ ሁለት ወራት የማሰቢያ ጊዜ ገደብ ተሰጥቶ ነበር፡፡

አሜሪካ ቀድሞ ያሳወቀችው የአጎዋ እድል ስረዛን በተመለከተ ውሳኔዋን እንድቀለብስ የአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል እና አድቮከሲ ኔትወርክ የማግባባት ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

የአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባሏ እና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ካረን ባስ የኢትዮጵያ ከአጎዋ መሰረዝ ዳግም እንዲጤን ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀው ነበር፡፡

ካረን ባስ ከቀናት በፊት በተመሳሳይ ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ላይ የተላለፈው የአጎዋ እገዳ ውሳኔ የኢትዮጵያ ህዝብና መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱ አሜሪካውያን ደክመው ያመጡትን የምጣኔ ሀብት እድገት ይቀለብሳል ብለው ነበር፡፡

የአሜሪካ መንግስት የአጎዋ እድሉን መሠረዙን ቀድሞ ባሳወቀበት የጥቅምት ወር መጨረሻ ምላሽ ሰጥቶ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት፣ ውሳኔውን የተሳሳተና የአሜሪካ መንግሥት ለዜጎች ደህንንት ያለውን ቁርጠኝነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብሎት ነበር፡፡

መንግስት ጨምሮም ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት እድሉ ከ200 ሺሕ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ላይ ተፅእኖ እንደሚኖረው ጠቅሷል፡፡ ይኸው ተጽእኖ በተለይም ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሴቶች ላይ ጉዳቱ ይበረታል ያለ ሲሆን፣ በአቅርቦት ሰንሰለቱ የሚሳተፉትን የአንድ ሚሊዮን ነዋሪዎችን ሕይወት በእጅጉ እንደሚጎዳም ነው የገለጸው፡፡

የትግራይ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ የአጎዋ እድል እንዲሰረዝ በሕወሃት በሎቢ አድራጊነት የሚሠራው ቮን ባተንግ ሞንግዩ የተሰኘ ቡድን ሲሠራ ቆይቷል፡፡

በአንጻሩ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለማሰረዝ የሚንቀሳቀሰውን ቡድን ሐሳብ ለማክሸፍ ደግሞ ‹‹አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቴ›› የተሰኘ ሌላ ቡድን ሲሠራ የነበረ ቢሆንም፣ የባይደን አስተዳዳር ኢትዮጵያ ከቀናት በኋላ ከሚጀምረው የፈረንጆቹ ዐዲስ ዓመት ጀምሮ ሰርዟታል፡፡

አጎዋ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ቀጥረው የሚያሠሩ የውጭ አገር ባለሐብቶችና አልሚዎች፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ትልቁ ምክንያታቸው መሆኑን ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img