አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 14፣ 2014 ― የአሜሪካ ሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባል የሆኑት ካረን ባስ የኢትዮጵያ ከአጎዋ መሰረዝ ዳግም እንዲጤን ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
የአሜሪካው መንግስት የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል ማንሳቱን ያስታወቀው በጥቅምት ወር መገባደጃ ሲሆን፣ አገሪቱ የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል ያነሳችው ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የሰብአዊ ጥሰቶችን በመጥቀስ ነው።
ነገር ግን በሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ካረን ባስ፣ ከሴናተር ክሪስ ቫን ሆለን ጋር ባስገቡት ደብዳቤ ለሁሉም የጦርነቱ ተፋላሚ አካላት ግጭቱን እንዲፈቱ ጊዜ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የምክር ቤት አባሏ ካረን ባስ ከቀናት በፊት በተመሳሳይ ባወጡት መግለጫ በኢትዮጵያ ላይ የተላለፈው የአጎዋ እገዳ ውሳኔ የኢትዮጵያ ህዝብና መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱ አሜሪካውያን ደክመው ያመጡትን የምጣኔ ሀብት እድገት ይቀለብሳል ብለው ነበር፡፡
አያይዘውም ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን የህብረተሰ ክፍሎች ችግሮች ችግር እንደሚያብብስ ገልጸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ የአጎዋ እድል መሰረዝ ጋር በተገናኘ በተመሳሳይ የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል እና አድቮከሲ ኔትወርክ የኢትዮጵያን የአጎዋ እድል ለማስመለስ ጥረት ላይ መሆኑን ገልጿል።
ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የመጨረሻ ግፊት ይሆናል ያለውን ደብዳቤ ማስገባቱን የገለፀው ኔትወርኩ፣ ከሰሞኑ ከበርካታ ኮንግሬሽናል መሪዎች፣ ከዋይት ሃውስ ባለስልጣናት እንዲሁም ከጥቁር አሜሪካውያን የኮንግረስ መሪዎች እና የሴኔት መሪዎች ጋር ውይይት ማድረጉንም አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከአጎዋ መሰረዟ አገር ውስጥ የሚገኙት እንደ ካልቪን ክለይን፣ ቶሚ ሂልፊገር እና ኤችኤንድኤምን የመሳሰሉ በዓለም ታዋቂ አምራቾች መቆየታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ስለመሆኑም ቀድመው ስጋታቸውን የሚያጋሩ ነበሩ።