አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ታኅሣሥ 14፣ 2014 ― የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ላምሮት ከማል የተባለችው ግለሰብ ድምጻዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ በሽጉጥ በተመታበት ወቅት እርዳታ እንዲያገኝ ባለማድረግ በቸልተኝነት ወንጀል ጥፋተኛ ብሏታል፡፡
ላምሮትን ጥፋተኛ ያለው ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት በይደር የቀጠረ ሲሆን፣ የቅጣት ውሳኔ እስኪሰጥበት የነገው እለት ድረስ በፖሊስ ጣቢያ እንድትቆይ ትእዛዝ መተላለፉን ከችሎት ጉዳዮች ዘጋቢዋ ታሪክ አዱኛ ገጽ ተመልክተናል፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሿ ከአንድ የኦነግ ሸኔ አባል ጋር በሜክሲኮ አካባቢ በመገናኘት መንግስትን ከስልጣን ለማውረድ ታዋቂ ሰዎችን ለማስገደል ማቀዳቸውን እና ከነዚህ ታዋቂ ሰዎች መካከል አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ መሆኑን ግለሰቡ ገልጿላት ሀጫሉ እንዲገደል ቦታ እንድታመቻች በተነጋገሩት መሰረት የግድያ ቦታ አመቻችታለች ብሎ ክስ አቅርቧባት የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ግን የተከሰሰችበት ወንጀል በቂ ማስረጃ አልቀረበም ሲል በነጻ አሰናብቷት ነበር።
በውሳኔው ቅር የተሰኘው ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያለ ሲሆን፣ ይግባኙን የመረመረው የጠቅላይ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤት ነጻ በማለት የሰጠውን ውሳኔን በመሻር አርቲስት ሃጫሉ በሽጉጥ በተከሳሽ ጥላሁን ያሚ ተመትቶ ደም ሲፈሰው በቸልተኝነት እርዳታ እንዲያገኝ ባለማድረግ የወንጀል ህግ አንቀጽ 575 ንዑስ ቁጥር 1ን በመተላለፍ እንድትከላከል ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ከትእዛዙ በኋላ ተከሳሹዋ ለመደበኛው ፍርድ ቤት መከላከያ ማስረጃ የለኝም፤ ዓቃቤ ህግ ባሰማው ማስረጃ ይፈረድብኝ ማለቷን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ዕለት በቸልተኝነት ሰውን ባለ መርዳት በወንጀል ህግ አንቀጽ 575 ንዑስ ቁጥር 1ን በመተላለፍ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶባታል።
ተከሳሿ አንድ ገጽ የቅጣት ማቅለያ በጽሑፍ ያቀረበች ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ የቅጣች ማቅለያ ዛሬ ከሰዓት አቀርባለሁ ማለቱም ነው የተነገረው፡፡