አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 13፣ 2014 ― በቀጣዩ ጥር ወር ይፋ እንደሚደረግ ሲጠበቅ የነበረው ሁለተኛው የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ ለሌላ ጊዜ መዛወሩን የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ሁለተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ የወጣው መስከረም 18፣ 2014 ነበር።
ጨረታው በሒደት ላይ እንደነበር ያስታወሰው ባለሥልጣኑ፣ ከተጫራቾች በኩል የቀረቡ ጥያቄዎችን ተከትሎ ጨረታው እንዲዘገይ መደረጉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን ጨረታውን በቀጣይ በአጭር ጊዜ በድጋሚ ይፋ እንደሚያደርግ ከመጠቆም ውጪ፣ ትክክለኛ ጊዜውን አልጠቀሰም።
ከቀናት በፊት ጨረታውን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን የተናገሩት የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት በርካታ የምዕራባውያን ሚዲያዎችና ተቋማት፣ የፌደራል መንግሥት በሕወሓት ታጣቂዎች እየተሸነፈ የሚመስል መረጃ በመንዛታቸው፣ በኢንቨስተሮች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል ብለው ነበር።
መንግሥት ከዚህ ቀደም የቴሌኮሙዩኔኬሽን ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግ በወሰነው መሠረት፣ ዘርፉን የሚቀላቀሉ ሁለት ኩባንያዎች ለ15 ዓመታት አገልግሎቱን ማቅረብ የሚችሉበት ፈቃድ ለመስጠት በ2013 ባወጣው የመጀመሪያ ጨረታ ‹‹ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ›› የተባለው የኩባንያዎች ጥምረት አንደኛ አሸናፊ መሆኑም ይታወሳል፡፡