Tuesday, October 8, 2024
spot_img

በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ አባት ለጠ/ሚ ዐቢይ ግልጽ ደብዳቤ ጻፉ

በእስር ላይ የሚገኘው የአሐዱ ራድዮ የዜና ክፍል አርታኢ ጋዜጠኛ ክብሮም ወርቁ አባት አቶ ወርቁ አብርሃ ለጠቅላይ ሚኒስትቅ ዐቢይ አሕመድ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል።

የጋዜጠኛው አባት ፍ/ቤት ልጄን በዋስ እንዲወጣ ቢወስንለትም ፖሊስ ለመልቀቅ እምቢተኛ ሆኗል ሲሉ ነው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤት ያሉት።

ጋዜጠኛ ክብሮም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው በአርታኢነት በሚሰራበት አሐዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ተረኛ በነበረበት ቀን፤ በጣቢያው ጋዜጠኛ በተሰራ ዜና ምክንያት ነው።

ዜናው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የምትገኘው የሀይቅ ከተማ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሏን የሚገልጽ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ዜናውን የሰራችውን ሉዋም አታክልቲ እና አርታኢዋ ክብሮም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል። 

ጋዜጠኛ ሉዋም ዜናው በተላለፈበት ዕለት ጥቅምት 12፤ 2014 በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስትውል፣ የዜና አርታኢው ክብሮም ከአራት ቀናት በኋላ ታስሯል። ሉዋም ከ21 ቀናት እስር በኋላ ኅዳር 3፤ 2014 በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈትታለች።

ነገር ግን ክብሮም ወርቁ ያለበት ያልታወቀ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግን ከእስር መፍታቱን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።

የጋዜጠኛው ቤተሰቦች በበኩላቸው ክብሮም በፍርድ ቤት ከእስር እንዲለቀቀ ቢወሰንለትም እስካሁንም ያለበትን እንደማያውቁ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

የጋዜጠኛው አባት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ፣ ላለመለቀቁ “አንድ ነገር ሳልወድ በግድ ልቤን ይቆረቁረኛል” በማለት ምክንያቱ መጠሪያ ስሙ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል።

ክብሮም የሚለው ቃሉ የግዕዝ ነው ያሉት የጋዜጠኛው አባት፣ ግዕዝ ደግሞ የኢትዮጵያ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ስለሆነም ትግርኛ ተጋርቶታል ብለዋል።

ታድያ ልጄን “ክብሮም” ብዬ መሰየሜ ምንድን ነው ሃጥያቴ ሲሉ ጥያቄ የሰነዘሩት አባት፣ እርሱስ ቢሆን እኔ ባወጣሁለት ሥም ለምን ዋጋ ይከፍላል ብለዋል።

አቶ ወርቁ አብርሃ አያይዘውም ልጄን ሳሳድገውም ኢትዮጵያዊ አድርጌ እንጂ የብሄር ስነ ልቦናን አላብሼ አልነበረም ያሉ ሲሆን፣ በዚህ ደግሞ እንደሚኮሩ ገልፀዋል።

ልጃቸው ክብሮም አሸባሪ ሲሉ የጠሩት ህወሓት ተላላኪ ለመሆኑ ፖሊስ ቅንጣት (ሽርፍራፊ) ማስረጃ እንኳ ማቅረብ አለመቻሉን እንዲሁም አይችልም ሲሉ በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።

አቶ ወርቁ አብርሃ በደብዳቤያቸው ማሳረጊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለልጃቸው ፍርድ ቤት የሰጠው የዋስትና መብት ብቻ እንዲከበርለት እንዲያደርጉ ተማጽነዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img