አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 13፣ 2014 ― የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል እና አድቮከሲ ኔትወርክ የኢትዮጵያን የአጎዋ እድል ለማስመለስ ጥረት ላይ መሆኑን ገልጿል።
ለአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የመጨረሻ ግፊት ይሆናል ያለውን ደብዳቤ ማስገባቱን የገለፀው ኔትወርኩ፣ ከሰሞኑ ከበርካታ ኮንግሬሽናል መሪዎች፣ ከዋይት ሃውስ ባለስልጣናት እንዲሁም ከጥቁር አሜሪካውያን የኮንግረስ መሪዎች እና የሴኔት መሪዎች ጋር ውይይት ማድረጉንም አስታውቋል።
በውይይቱ ሁሉም አካላት ኢትዮጵያ አጎዋ የሚያተኩረው በዜጎች የእለት ተእለት የኑሮ እድል መሻሻል ላይ ስለሆነ ኢትዮጵያ መቀጠል እንዳለባት አረጋግጠውልናል ብሏል።
ኔትወርኩ ጆ ባይደንም እነዚህ መሪዎች የተናገሩትን ድምፅ በመስማት ድሃ ዜጎችን ከመጉዳት አሜሪካ እንድትቆጠብ እንዲያደርጉ ጠይቄያለሁ ሲል አመልክቷል።
ይህንኑ ደብዳቤ የዋይት ሃውስ ኦፊስ ኦፍ ፕሬዝዳንሻል ኮሮስፖንደንስ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ኤቫ ኬምፕ መቀበላቸውንም በሎቢ ድርጅቱ አማካኝነት ማረጋገጡን ጠቁሟል።
የአሜሪካው መንግስት የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል ማንሳቱን ያስታወቀው በጥቅምት ወር መገባደጃ ነበር።
አገሪቱ የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል ያነሳችው ከትግራይ ጦርነት ጋር ተፈጽመዋል የሰብአዊ ጥሰቶችን በመጥቀስ ነው።