አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 13፣ 2014 ― በደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ በምትገኘው የደብረታቦር ከተማ ከጀምበር ማዘቅዘቅ በኋላ የሚሰማ የተኩስ ድምጽ ነዋሪዎችን ማስመረሩ ተነግሯል፡፡
አዲስ ዘይቤ ድረ ገጽ ባስነበበው ዘገባ፣ ‹‹ክስተቱ በቅርብ ጊዜ የተጀመረ አይደለም›› የሚሉት ነዋሪዎች፣ ‹‹ቀደም ሲል ጋብ ብሎ ነበር፤ አሁን እንደገና ብሶበታል›› ማለታቸው ተመላክቷል፡፡
ነዋሪዎቹ ከምሽት ጀምሮ ሌሊቱን የሚደመጠው ተኩስ ከሦስት ዓመት በፊትም እንዳጋጠመና አሁን ተባብሶ እንደሚደመጥ ነው የገለጹት፡፡
የደቡብ ጎንደር ዞን የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር የሰላምና የሕዝብ ደህንነት ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽባባው ሞላ በበኩላቸው ይህን መሰል ድርጊት ይበልጥ የተስፋፋው ከ2008 ጀምሮ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የቀበሌ መዋቅሩ፣ የከተማ አስተዳደሩ፣ የፖሊስ አባላት፣ የአድማ ብተና፣ የሚሊሻ ኃይሎቻችን በመቀናጀት እየሰራን ነው ያሉት ኃላፊው፣ አላግባብ የሚተኩሱትን ከማስቀጣት በተጨማሪም ከፖሊስ አካላት ውጪ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እያገድን ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በአካባቢው በሚተኮሰው ጥይት በቀብር ስነ ስርአት ላይ የለቀስተኞችን ህይወት ያጠፋበት አጋጣሚ ስለመኖሩም የተጠቀሰ ቢሆንም፣ ችግሩ ተከስቷል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የተስፋፋበት ምክንያት በግልጽ እንደማይታወቅም ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡