Friday, November 29, 2024
spot_img

መንግሥት ሕወሓትን ለማሳደድ በትግራይ መንደሮችና ከተሞች ውስጥ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የማካሄድ ፍላጎት የለውም ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 13 2014 ― የፌዴደራል መንግሥት ሕወሓትን ለማሳደድ በትግራይ ውስጥ በሚገኙ በእያንዳንዱ መንደሮችና ከተሞች ውስጥ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የማካሄድ ፍለጎት እንደሌለው የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን ናቸው፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ይህን የተናገሩት ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮች ስለ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

አምባሳደር ሬድዋን በማብራሪያቸው ሕወሓት ከዚህ በኋላ ምንም ዐይነት ጥቃት መፈጸም እንዳይችል ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ ነገር መንግሥት እንደሚያደርግ መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

አያይዘውም መንግሥት የአገሪቱን የግዛት አንድነት የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ያለውን መብት ተግባራዊ እንደሚያደርግ የገለጹት አቶ ሬድዋን፣ ትግራይን ጨምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የፈደራሉን ሠራዊት የማሰማራት መብቱን እንደሚያስከብር ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በሰጡት ወቅት የሕወሓት ተዋጊዎች ይዘዋቸው ከነበሩ አካባቢዎች ለሰላም ስንል ለቅቀን ወጥተናል ማለታቸውን በተመለከተም የተናገሩ ሲሆን፣ የሕወሓት ተዋጊዎች የለቀቁት ለሰላም ካላቸው ፍላጎት ሳይሆን ከባድ ሽንፈት ገጥሟቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አስራ ሦስት ወራት ባስቆጠረው የፌዴራል መንግስት እና የሕወሓት ጦርነት ባለፉት ሳምንታት የአገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች ኃይሎች የሕወሃት ተዋጊዎች ይዘዋቸው የቆዩ በርካታ የአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎችን ማስለቀቃቸው መነገሩ አይዘነጋም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img