- የተመዘገበው ቁጥር ከ5 ወራት ገደማ ወዲህ ከፍተኛው ነው
አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ታኅሣሥ 13፣ 2014 ― በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ብቻ ከ2 ሺሕ በላይ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር መመዝገቡን የጤና ሚኒስቴር በትላንትናው እለት ምሽት ያወጣው እለታዊ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ትላንት በወጣው ሪፖርት የተመዘገበው 2 ሺሕ 323 በኮሮና የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ነሐሴ 19፣ 2013 ከተመዘገበው 2 ሺ 19 ሰዎች ቁጥር ወዲህ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በዓለማችን ከተከሰተ ሁለት ዓመት ያስቆጠረው የኮሮና ቫይረስ፣ በመላው ዓለም ከ276 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ሲያጠቃ ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ሕይወት ቀጥፏል፡፡
ቫይረሱ ዐይነቱን እየቀያየረ በአሁኑ ጊዜ በርካታ የዓለም አገራት ከሁሉም የከፋ ነው የተባለለት ኦሚክሮን የሚል ሥያሜ የተሰጠውን ልውጥ እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን አዲሱ ኦሚክሮን በኢትዮጵያ መታየቱን የጤና ሚኒስቴር ያሳወቀው ነገር የለም፡፡
በአገራችን እስከ ትላንትናው እለት ድረስ ከ379 ሺሕ በላይ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል 6 ሺሕ 877 ሰዎች ላይመለሱ አሸልበዋል፡፡ ቫይረሱ በትላናትናው እለት ብቻ የ5 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡