አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 19፣ 2013 ― በኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ሃያ ሰዎችን መግደላቸው ተነግሯል፡፡
ጥቃቱ ዐርብ ሚያዝያ 15 ሊሙ ኮሳ ወረዳ፣ ቀጮ ክርክራ እና ጋሌ በተባሉ ቀበሌዎች ውስጥ የተፈጸመ ሲሆን፣ ቢያንስ 20 ንጹሐን ዜጎች መገደላቸውን ቢቢሲ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አረጋግጫለሁ ብሎ ዘግቧል፡፡
ኮሚሽኑ ከአካባቢው ባሰባሰበው መረጃ በጂማ ዞን የተፈጸመው ጥቃት የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የሚያመለክት መረጃ እንዳገኘ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ኢማድ ቱኔ ገልጸዋል፡፡
አቶ ኢማድ ቱኔ አክለውም በጅማ ዞን ሊሙ ኮሳ ወረዳ ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች የደረሱት ታጣቂዎቹ ጥቃት ፈጽመው በሥፍራው በርካታ ንጹሐን ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነው።በተመሳሳይ ከዚያ ቀደም ባለው ቀን ሐሙስ ሚያዝያ 14 በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ፣ ዳኖ ቀበሌ ውስጥ በታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሰው መገደሉንም ኮሚሽኑ ጨምሮ አመልክቷል።
በዚህ ጥቃት የተገደለው ግለሰብ ከብት ጥበቃ ላይ የነበረ ነው የተባለ ሲሆን፣ ከ70 በላይ ከብቶች በታጣቂዎቹ ተነድተው መወሰዳቸውም ተነግሯል፡፡
ኢሰመኮ ከሰሞኑ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በንጹሐን ላይ ጥቃት መደጋገሙን በማመልከት በነዋሪዎች ላይ የሚደርስ ተጨማሪ ጉዳትና የሰዎች ሞት ለመከላከል አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ያሳሰበ ሲሆን፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ተደጋጋሚነት እና መስፋፋት የፀጥታ መዋቅሩ የመከላከል እና ዝግጁነት አቅም ከፍተኛ መሻሻል ሊደረግበት እንደሚገባም የሚጠቁም ነው ብሎ ነበር።
[/et_pb_text][/et_pb_column][/et_pb_row][/et_pb_section]