Thursday, November 28, 2024
spot_img

አዲስ ስታንዳርድ በመንግሥታዊው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መሠረተ ቢስ ውንጀላ እና አደገኛ ሥም ማጥፋት ተካሄዶብኛል አለ

 

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 12፣ 2014 ― አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው ድረ ገጽ በመንግሥታዊው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መሠረተ ቢስ ውንጀላ እና አደገኛ ሥም ማጥፋት ተካሄዶብኛል ሲል ወቀሳ አቅርቧል፡፡

የድረ ገጹ ባለቤት ጃኬን አሳታሚ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር አዲስ ስታንዳርድን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ለአጭር ጊዜ እንዲታገድ ማድረጉን ተከትሎ ፋና ‹‹አዲስ ስታንዳርድ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አጀንዳ ተግባራዊ በማድረግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተላልፏል›› በማለት ‹‹በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ ዘገባ›› አሰራጭቶብኛል ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ታኅሣሥ 10፣ 2014 ፋና አዲስ ስታንዳርድን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር ከአሜሪካ መንግስት ገንዘብ እየተቀበለ ነው የሚል ዘገባ እንደሠራበት አስታውቋል፡፡

ይህ ዘገባ መሠራጨቱን ተከትሎም የዜና ክፍል አባላቱ ላይ የግድያ ዛቻን ጨምሮ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች አስደንጋጭ ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑንም ለጣቢያው በጻፈው ደብዳቤው አመልክቷል፡፡  

ከዚህ በተጨማሪም ፋና በአዲስ ስታንዳርድ ከዓለም አቀፍ የስለላ መረብ ኤጀንሲዎች ጋር ግንኙነት አለው የሚል ዘጋቢ ፊልም ተሰርቶበታል ያለው አሳታሚው፣ በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርብ የሥም ማጥፋት የፍትሐ ብሔር ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በማስታወስ፣ በሕጉ መሠረት ተመጣጣኝ እርማት ይሰጥልኝ ሲል ጠይቋል፡፡

ከጣቢያው ውጭ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ማህበር በፋና የሚሠራጩ እና ሠራተኞቻችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን በመቆጣጠር በኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ ጥበቃ ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት ያግዝ ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ፋና እሑድ ታኅሣሥ 10፣ 2014 በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው ዘገባ አዲስ ስታንዳርድ በዴሞክራሲ ማስፋፋት ስም ከአሜሪካው ‹‹ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ›› በፈረንጆቹ 2019 ብቻ 75 ሺሕ 990 ዶላር ተቀብሏል ብሏል፡፡    

 

 

አዲስ ስታንዳርድ የፋና ዘገባ መሠረተ ቢስ ነው ቢልም፣ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እስካሁን ድረስ ተጨማሪ ማብራሪያም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም፡፡

ጃኬን በተሰኘ አሳታሚ በየካቲት 2003 የተመሰረተው አዲስ ስታንዳርድ፣ ከዚህ ቀደም በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚታተም መጽሔቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ የመጽሔቱ ኅትመት በ2009 ከቆመ በኋላ በድረ ገጽ ብቻ ተወስኖ ቆይቷል፡፡

ድረ ገጹ በሥፋት ከሚታወቅበት የእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞ እና አማርኛ ቋንቋዎችን በመጨመር ከትላንት ታኅሣሥ 11፣ 2014 ጀምሮ ባለሦስት ቋንቋ ድረ ገጽ ይፋ አድርጓል፡፡

 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img